አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪን አሰልጣኝ አድርጎ ለአንድ ዓመት በመቅጠር በወረደበት ዓመት ወደ ፕሪምየር ሊግ የመመለስ አላማን የያዘው አርባምንጭ ከተማ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የሁለት ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል። ሰባት ተጫዋቾችን ደግሞ ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ አሳድጓል፡፡
የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ታዲዮን ጨመሳ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት ከሆነ በቀጣዩ ዓመት ወደ ሊጉ ለመመለስ ከወዲሁ በሚገባ ስራቸውን እንደሚሰሩና ተጫዋቾችን ማስፈረም የዚህ አካል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪም በርግጠኝነት ቡድኑን ዳግም ለመመለስ ቆርጠው እንደተነሱ ገልፀዋል፡፡
የቀድሞው የወላይታ ድቻ አጥቂ እና ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታትን በሀላባ ከተማ ያሳለፈው፤ በዘንድሮው የከፍተኛ ሊግ ለሀላባ ከተማ 16 ግቦችን በማስቆጠር በፕሪምየር ሊግ ክለቦች ዓይን ውስጥ ገብቶ የነበረው አጥቂው ስንታየሁ መንግስቱ የቀድሞው አሰልጣኙን መሳይ ተፈሪን ተከትሎ በአንድ ዓመት ውል ተቀላቅሏል፡፡
አርባምንጭ ከተማ በተጨማሪነትም የሀዲያ ሆሳዕና ከተማውን የመስመር ተከላካይ በረከት ወልደ ዮሀንስን ሲያስፈርም በከፋ ቡና ጥሩ የውድድር ዓመትን ያሳለፈው ግብ ጠባቂው ሰይድ ሐብታሙ እና የኮንሶ ኒውዮርኩ ግብ ጠባቂ ይስሀቅ ተገኝ ክለቡን በአንድ ዓመት ውል ተቀላቅለዋል፡፡
ክለቡ ተጨማሪ ተጫዋቾችን በቀጣይ ቀናት ለማስፈረም ጥረት እንደሚያደርግ ሲገለፅ የተከላካዮቹን ወርቅይታደስ አበበ እና አንድነት አዳነን ውል ለአንድ ዓመት ያራዘሙ ሲሆን ከ20 ዓመት በታች ቡድን ደግሞ ሰባት ተጫዋቾችን ክለቡ አሳድጎል፡፡