ረጅም ወራትን ከጨዋታ ርቆ የቆየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ በሀዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በ10:00 ላይ የቡሩንዲ አቻውን በወዳጅነት ጨዋታ ይገጥማል።
በ2019 በካሜሩን አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ሁለተኛ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች በቀጣይ ሳምንት ሲካሄዱ ከጋና ሴራሊዮን እና ኬኒያ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጳጉሜ 4 ሴራሊዮንን ሀዋሳ ላይ ያስተናግዳል። ያለፉትን 25 ቀናት በሀዋሳ ዝግጅት እያደረገ የሚገኘው ብሔራዊ ቡድኑ ለወሳኙ የማጣሪያ ጨዋታ ይረዳው ዘንድ ዛሬ (ዕሁድ) ከቀኑ በ10:00 ከብሩንዲ ብሔራዊ ቡድን ጋር ይጫወታል። በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የሚመራው ቡድኑ ከዛሬው ጨዋታ በፊት ትላንት ረፋድ 4 ሰአት ላይ ልምምድ ያደረገ ሲሆን አምሳሉ ጥላሁን፣ እስራኤል እሸቱ፣ ተመስገን ካስትሮ፣ በዛብህ መለዮ፣ ዐወት ገ/ሚካኤል፣ በኃይሉ አሰፋ እና አቤል ማሞ በጉዳት ከወዳጅነት መርሀግብሩ ውጭ ሲሀኑ ሰሞኑን ጉዳት ላይ የነበረው አህመድ ረሺድ ለጨዋታው ብቁ ነው ተብሏል። በውጪ ሀገር እየተጫወቱ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል ደግሞ የፔትሮጄቱ ሽመልስ በቀለ ቡድኑን የተቀላቀለ ተጫቸች ነው።
ትላንት አዲስ አበባ የገባው የብሩንዲ ብሔራዊ ቡድን አመሻሹን ሀዋሳ ሲደርስ በሌዊ ሪዞርት ማረፊያውን ያደረገ ሲሆነ ልምምድን በዛው በሆቴል አካባቢ ምሽት አንድ ሰአት ገደማ አከናውኗል። 24 የልዑካን ቡድን አባላትን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ብሔራዊ ቡድኑ ግማሽ ወጪው በኢትዮጵያ እግር ኳር ፌድሬሽን እንደተሸፈነለት ሰምተናል።
ጨዋታውን ኢትዮጵያውያን ኢንተርናሽናል ዳኞች ሲመሩት በዋና ዳኝነት ብሩክ የማነ ብርሀን፣ በረዳትነት ክንዴ ሙሴ እና ትግል ግዛው፣ አራተኛ ዳኛ ደግሞ ፌድራል ዳኛ ሶሬሳ ካሚል መሆናቸው ታውቋል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኙት ህዳር 28 ቀን 2010 በሴካፋ ውድድር ላይ ሲሆን ቡሩንዲ 4-1 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።