ከቀናት በፊት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በቃል ደረጃ የተስማማው ኢስማኤል ዋቴንጋ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ፊርማውን ማኖሩን ክለቡ በፌስቡክ ገፁ ይፋ አድርጓል።
ኢትዮጵያ ቡና ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት አገልግሎት የሰጠው ቤኒናዊው ግብ ጠባቂ ሀሪስተን ሄሱን ካሰናበተ በኋላ ተተኪ ግብ ጠባቂ ሲያፈላልግ የቆየ ሲሆን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ነበር ከኢስማኤል ዋቴንጋ ጋር ከስምምነት መድረስ የቻለው። ግብ ጠባቂው በትላንትናው እለት አዲስ አበባ በመምጣት ከቡድኑ ጋር የሁለት ዓመት ውል መፈራረሙ ታውቋል። ነገ ጠዋት በፌዴሬሽን በመገኘትም ውሉ ይፀድቃል ተብሏል።
ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ በሀገሩ ክለብ ቫይፐርስ ከ2013 ጀምሮ የቆየ ሲሆን ለዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን በበርካታ ጊዜያት ተመርጦ ተጫውቷል። በተለይ በ2015 ኢትዮጵያ ላይ ተስተናግዶ በነበረው የምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ላይ ሀገሩን ለቻምፒዮንነት ያበቃ ሲሆን የውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂ ተብሎ መመረጡ የሚታወስ ነው። ዋቴንጋ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ከተጫወቱት ዴኒስ ኦኒያንጎ፣ ካሊሱቡላ ሀኒንግተን እና ሮበርት ኦዶንካራ በመቀጠል አራኛው ዩጋንዳዊ ግብ ጠባቂ ይሆናል።
በክረምቱ በርካታ ተጫዋቾችን የለቀቀው ኢትዮጵያ ቡና እስካሁን 5 ተጫዋቾችን ሲያስፈርም ሁለቱ የውጪ ዜግነት ያላቸው ናቸው። የሁለት የውጪ ተጫዋቾች ኮታ የሚቀረው ቡና በቀጣይ ሱሌይማን ሎኮዋ የተባለ ኮንጓዊ አጥቂ እንደሚያስፈርም በፌስቡክ ገፁ አስታውቋል።