የኢትዮጵያ ዋንጫ| ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን በመርታት ወደ ግማሽ ፍፃሜው አልፏል

በ2010 መጠናቀቅ የነበረበት የኢትዮጵያ ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) ወደ ዘንድሮው ዓመት ተሸጋግሮ ዛሬ መደረግ ሲጀምር በውድድር ዓመቱ የመጀመርያ የነጥብ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሲዳማ ቡና ተገናኝተው ፈረሰኞቹ በመለያ ምት በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ተሸጋግረዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላይታ ድቻን በመርታት ወደ ሩብ ፍፃሜ ያለፈ ሲሆን ሲዳማ ቡና ደግሞ ሀዋሳ ከተማን በመርታት ነበር ለዚህ ጨዋታ የቀረበው። ጨዋታው በአዲስ የውድድር ዓመት እንደመደረጉ ክለቦቹም አዳዲስ ተጫዋቾቻቸውን ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ጌታነህ ከበደ እና አቤል ያለው በቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አበባየሁ ዮሀንስ በሲዳማ ቡና ማልያ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ወደ ሲዳማ ቡና የተመለሱት ጸጋዬ ባልቻ (ከስድስት ወር ውሰት) እና ሰንደይ ሙቱኩም ለመጀመርያ ጊዜ ጨዋታ አድርገዋል።

በበርካታ ተመልካች እና ከባድ ዝናብ ታጅቦ የተደረገው ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ያስተናገደ ቢሆንም የግብ እድሎች እምብዛም ያልተመለከትንበት ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሲዳማ ቡናዎች በሐብታሙ ገዛኸኝ አማካኝነት ጥሩ የማግባት አጋጣሚ ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ከቀሩ በኋላ ሁለቱም ክለቦች ከጠሩ የግብ እድሎች ርቀው ይልቁንም ኃይልን መሠረት ያደረገ አጨዋወትን ሲከተሉ ተስተውሏል። ለዚህም በመስመር በኩል አዲስ ግደይ እና አብዱልከሪም መሀመድ እንዲሁም ዮሴፍ ዮሀንስ እና በኃይሉ አሰፋ ሲፈጥሩት የነበረው ፍትጊያ እንዲሁም ወንድሜነህ ዓይናለም በ18ኛው ደቂቃ በጉዳት ተቀይሮ መውጣቱ እንደ ማሳያ የሚቆጠሩ ናቸው። በሙከራ ረገድ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ጌታነህ ከበደ እና ናትናኤል ዘለቀ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ግብ ተጠግተው ለአቤል ያለው የፈጠሩትን እድል አቤል ሳይጠቀምበት የቀረው እና 41ኛ ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ዮሀንስ አክርሮ መትቶ ለአለም ሲተፋው ሀብታሙ አግኝቷት በቀላሉ ያመከናት እድል በሲዳማ በኩል ሊጠቀሱ የሚችሉ የመጀመሪያ አጋማሽ እድሎች ናቸው።


በሁለተኛው አጋማሽ ተመሳሳይ እንቅስቃሴን ተመልክተናል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ላይ አዲስ ግደይ በሚገባ ያሳለፈለትን ኳስ ሐብታሙ ገዛኸኝ አክርሮ መትቶ ቋሚው ብረት ሲመልስበት 58ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ዮሴፍ የሰጠውን ኳስ አዲስ ግደይ ቢያገኛትም አስቻለው ታመነ በአስደናቂ መልኩ ያወጣበት በሲዳማ በኩል፤ 65ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ አሰፋ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ጌታነህ ከበደ በግንባሩ ገጭቶ ከግብ መስመሩ ላይ ትርታዬ ደመቀ ያወጣት እና ተቀይሮ የገባው አቡበከር ሳኒ በሁለት አጋጣሚዎች የፈጠራቸው የግብ እድሎች በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የሚጠቀሱ ናቸው።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በዚህ መልኩ ያለ ግብ በመጠናቀቁ በቀጥታ ወደ መለያ ምቶች አምርተዋል። እስከ ስምንተኛ ምት በደረሰው መለያ ምት ሙሉዓለም መስፍን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሲያመክን ዮሴፍ ዮሀንስ እና ፈቱዲን ጀማል ከሲዳማ ቡና አምክነው ፈረሰኞቹ 7-6 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ተሸጋግረዋል።

የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች በመጪው ማክሰኞ ሀዋሳ ላይ ሲከናወኑ 08:00 ኢትዮጵያ ቡና ከመከላከያ፣ በ10:00 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ጅማ አባ ጅፋር የሚጫወቱ ይሆናል። ቅዳሜ በሚጠናቀቀው ውድድር ቻምፒዮን የሚሆነው ክለብ ከህዳር እስከ ግንቦት ድረስ በሚከናወነው የ2018/19 ካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ይሳተፋል።