የሶዶ ስታዲየም የመጀመርያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን አስተናግዶ ከህዳር በኋላ ለእድሳት ይዘጋል። እድሳቱ እስከሚጠናቀቅም በቦዲቲ ሜዳ እንደሚጫወት ክለቡ አስታውቋል፡፡
በሊጉ በርካታ ክለቦች የሜዳውን አመቺ አለመሆንን በተደጋጋሚ በቅሬታ መልክ ሲገልፁ የሚስተዋለው የሶዶ ስታዲየም ክረምቱ በገባ ቁጥር በተደጋጋሚ እየታደሰ ቢቆይም ችግሮቹ ሲቀረፉ አልተስተዋለም። በዚህም ምክንያት የቦዲቲ ስታድየምን በአማራጭነት ሲጠቀም ቆይቷል። ይህን ተከትሎም ክለቡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ስታዲየሙን በዘመናዊ መልኩ ገንብቶ ለውድድር ለማብቃት ጥረት ላይ መሆኑን የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ሆሲሶ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡ እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ ከሆነ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ጨዋታዎችን በሶዶ ስታዲየም ካደረገ በኋላ ለእድሳት የሚዘጋ ሲሆን ወደ ቦዲቲ ስታዲየም በማምራት የሊግ ጨዋታዎችን የሚያደርግ ይሆናል። የሶዶ ስታዲየምም የመቀመጫ ወንበሮች፣ በአዲስ መልክ ሳር የማልበስ እንዲሁም የመልበሻ ክፍል ግንባታዎችን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች ይሰራሉ።
ክለቡ እድሳቱ እስከሚጠናቀቅ ጨዋታ የሚያደርግበት የቦዲቲ ስታድየም የመቀመጫ ወንበር እና የመጫወቻ ሜዳን አመቺ ለማድረግ በቀጣይ ቀናት የመጠገን ስራዎች እንደሚሰሩ ስራ አስኪያጁ ጨምረው ገልፀዋል።
ፎቶዎች – ከላይ የሶዶ፤ ከታች የቦዲቲ ስታድየሞች ወቅታዊ ገፅታ