የትግራይ ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው ወደ ቀጣይ ዙር ያለፉ እና ከምድብ የተሰናበቱ ቡድኖች ተለይተው ታውቀዋል። ከምድብ 1 ሽረ እንዳሥላሴ እና ደደቢት ወደ ቀጣዩ ዙር ሲያልፉ ወልዋሎ ከምድቡ ተሰናብቷል። ከምድብ 2 ደግሞ መቐለ እና ድሬዳዋ ወደ ቀጣዩ ዙር ሲያልፉ አክሱም ከተማ ምድቡ ተሰናባች ሆኗል።
በ8 ሰዓት የጀመረው እና ብዙ ማራኪ ጨዋታ ባልታየበት የደደቢት እና የሽረ የምድብ ሀ የመጨረሻ ጨዋታ ሽረ 2-1 አሸንፏል። የደደቢት የጨዋታ የበላይነት በታየበት የመጀመርያው አጋማሽ ጨዋታው ከግማሽ ሰዓት በላይ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳይደረግበት የቆየ ሲሆን በአመዛኙ በመሀል ሜዳ የሚቆራረጥ እና አሰልቺ እንቅስቃሴ በርክተውበት ተስተውልዋል። በ 3-5-2 ወደ ሜዳ የገቡት ሽረዎች ሁለቱ የመስመር ተከላካዮቻቸው ሙሉጌታ ዓምዶም እና ጅላሎ ሻፊ በኣመዛኙ በበርካታ ክፍለ ግዜ ከራሳቸው ሜዳ ክልል ነቅለው ሙሉ በሙሉ በማጥቃቱ ወረዳ መገኘታቸውና ቡድኑ ከተፈጥራዊ የአማካይ ተከላካይ ውጭ መግባቱ ተደምሮበት በተደጋጋሚ ሚዛኑን ሲያጣ እና ለመልሶ ማጥቃት ሲጋለጥ ታይቷል። በ 35ኛው ደቂቃ ሽረዎች ሰለሞን ገ/መድህን ባረገው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲያደረረጉ በመጀመርያው አጋማሽ መገባደጃ ኪዳኔ አሰፋ ከቅጣት ምት ለጎል የቀረበ ሙከራ አድርጎ ነበር። ከሽረ አንፃር ሲታይ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ያሳዩት ደደቢቶች እንደወሰዱት ብልጫ ብዙም የጠራ ሙከራ ባያረጉም በሁለት የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች እጅግ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም እንዳለ ከበደ ከግብ ጠባቂው ሰንደይ ሮቴሚ ተገናኝንቶ ያመከነው ይጠቀሳል።
በሁለተኛው አጋማሽ የመከላከል ባህሪ ያለው አሸናፊ እንዳለ እና ንስሃ ታፈሰ ቀይረው ካስገቡ በኋላ የጨዋታው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱት ሽረዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በርካታ የጎል እድሎች አምክነዋል። በተለይም ኪዳኔ ያመቻቸለትን ኳስ ተጠቅሞ ንስሃ ታፈሰ መቶ ተከላካዮች ተደርበው ያወጡበት እና ሙልጌታ አምዶም ያመከነው ኳስ ይጠቀሳሉ። ከመጀመርያው አጋማሽ ሲነፃፀር የተቀዛቀዙት ደደቢቶች በ 57 ደቂቃ ላይ በዓለምአንተ ካሳ ቀዳሚ የሚሆኑበት ጎል አስቆጥረው ጨዋታው መምራት ቢጀምሩም ብዙም ሳይቆዩ ሽረዎች በ 65ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ በገባው ንስሃ ታፈሰ ጎል አስቆጥረው አቻ መሆን ችለዋል። በ 65ኛው ደቂቃ ደግሞ ሰዒድ ሃሰን ሁለተኛውን አክሎ ጨዋታወ በሽረ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
10:00 ላይ አክሱም እና ድሬዳዋ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ሳቢ ባልነበረውና 2 ኢላማቸው የጠበቁ ሙከራዎች ብቻ በተመዘገቡበት የመጀመርያው አጋማሽ ጨዋታ አክሱሞች ፈጣን በሆኑት የፊት መስመር ተሰላፊዎች ተጠቅመው የድሬዳዋ ተከላካዮች ቢረብሹም ስለሺ ዘሪሁን ካደረጋት ለግብ የቀረበች ሙከራ ውጭ የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም። ከባለፈው ጨዋታ ሲነፃፀር ወርደው የቀረቡት ድሬዳዋዎች በመጀመርያው አጋማሽ በአክሱም የጨዋታ ብልጫ ቢወሰድባቸውም የተሻለ የጎል እድሎች ፈጥረዋል. በተለይም ኃይሌ ከረጅም ርቀት መትቶ ሙሴ ዮሃንስ ያዳነበት እና ወሰኑ ከቅጣት ምት ያደረጓቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። በመጀመርያው አጋማሽ በድሬዳዋ በኩል በተከላካይ አማካይነት የተሰለፉት ፍሬድ ሙሸንዲ እና ወሰኑ ማዜ በጥልቀት ወደ ኋላ በመሳብ ከተከላካዮች በቅርብ ርቀት መጫወታቸው ተከትሎ በአጥቂ ኣማካይ የተሰለፉት ተጫዋቾች ከቡድኑ እንዲነጠሉ አድርጓቸዋል። በተለይም በ10 ቁጥር ሚና የተጫወተው ኤታሙኔ ኬሜይኒ የዚህ ሰለባ ነበር።
ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ፉክክር በታየበት ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ የኳስ ፍሰት የታየበትም ነበር። ከቴዎድሮስ መንገሻ የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ልዑልሰገድ አስፋው መትቶ ብረቱ ገጭታ በተመለሰችበት ሙከራ ተነቃቅተው የጀመሩት አክሱሞች ጥረታቸው ሰምሮ በ56ኛው ደቂቃ ላይ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ተጠቅሞ ልዑልሰገድ አስፋው አስቆጥሮ አክሱምን መሪ ማድረግ ችሏል። ከጎሉ በኋላም አጥቅተው መጫወታቸውን የቀጠሉት አክሱሞች በቴዎድሮስ መንገሻ ሁለት ያለቀላቸው እድሎች አምክነዋል። ተጫዋቹ የተከላካዮች ስህተት ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው ፍሬው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከነው አስቆጪ ነበር።
አክሱሞች ጎል ካገቡ በኋላ በእጃቸው የገባውን መሪነት ለማስጠበቅ በጥልቀት በመከላከል እና ሰዓት በማባከን ሲጫወቱ ድሬዎች አጥቅተው ተጫውተዋል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ብዙ የጎል እድል ያመከኑት ድሬዎች ሲላ አብዱላሂ የአክሱም ተከላካዮች ከጨዋታ ውጭ ነው ብለው በተዘናጉበት ወቅብ ብቻውን ከግብ ጠባቂው ሙሴ ዮሃንስ ጋር ቢገናኝም ሙሴ በሚያስደንቅ ብቃት አድኖታል። በ 85ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገለችለትን ኳስ ተጠቅሞ ሲላ አብደላሂ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ አድርጎ ከዛ በኋላ ጨዋታው ምንም ሙከራ ሳያስተናግድ ተጠናቋል።
የምድብ ጨዋታዎቹን መጠናቀቅ ተከትሎ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች በመጪው አርብ ጥቅምት ሁለት ሲደረጉ 08:00 ላይ ሽረ እንዳሥላሴ ከ ድሬዳዋ ከተማ፤ በ10;00 መቐለ ከተማ ከ ደደቢት ለፍፃሜ ለማለፍ ይጫወታሉ።