አዳማ ከተማ ባለፈው ሳምንት በቃል ደረጃ የተስማማው ዩጋንዳዊው ግዙፍ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦንዶካራን አስፈርሟል።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት አራት ተጨዋቾችን ከፕሪምየር ሊግ ስድስት ተጨዋቾችን ደግሞ ከከፍተኛ ሊግ ያስፈረመው አዳማ ከተማ ለዘንድሮው የመጀመሪያ በአጠቃላይ ደግሞ ከኢስማኤል ሳንጋሪ በመቀጠል ሁለተኛ የውጪ ሀገር ዜግነት ያለው ተጫዋች አስፈርሟል። በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበረው ክለቡ በግብ ጠባቂዎች ስህተት ግቦች ሲያስተናግድ እንደነበር የሚታወስ ነው። ይህን ደካማ ጎኑን ወደ ሊጉ ይዞ ላለመግባትም ሁነኛ ግብ ጠባቂ ሲያፈላልግ ቆይቶ በመጨረሻም በሊጉ የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው ሮበርት ኦዶንካራ ላይ አርፏል።
በ2003 አጋሓሽ ዩጋንዳ ሪቬይኑ አውቶሪቲን ለቆ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀላቀል ላለፉት ሰባት ዐመታት የፈረሰኞቹን በር የጠበቀው ሮበርት በቅዱስ ጊዮርጊስ ስኬቶች ውስጥ ቁልፍ ሚና ነበረው። ግብ ጠባቂው ለ4 ተከታታይ ዓመታት (ከ2005-2008) የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኮከብ ግብ ጠባቂ ተብሎ ከመመረጡ ባሻገር ከ2003-2004 ድረስ ከ1500 በላይ ደቂቃዎች ጎል ሳይቆጠርበት በመቆየት የሊጉን ሪከርድ የጨበጠ ግብ ጠባቂ ነው።
የሮበርትን ወደ አዳማ ማምራት ተከትሎ ላለፉት ሶስት ዓመታት ክለቡን በግብ ጠባቂነት ያገለገለለው ዲሞክራቲክ ኮንጎዋዊው ጃኮ ፔንዜ ወደ ወልዋሎ ዓ.ዩ ያመራል ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም ግን ወልዋሎ ሶሪ ኢብራሂም የተባለ የማሊ ዜግነት ካለው ግብ ጠበቂ እየተደራደረ መሆኑም ተነግሯል።