በትግራይ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ እና መቐለ 70 እንደርታ ወደ ፍፃሜ ማለፍ ችለዋል።
7፡30 የተጀመረው የድሬዳዋ እና የሽረ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ መልካም እንቅስቃሴ የታየበት ሆኖ ሲያልፍ ብርቱካናማዎቹ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ እና በግብ ሙከራ የተሻሉ ነበሩ። አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ አምና በመቐለ እንዳሳዩት ቡድን በሚመሳሰል መልኩ በድሬዳው ከተማም በቀላሉ ግብ ማያስተናግድ እና በራሱ የሜዳ ክፍል ለተጋጣሚ ተጫዋቾች ክፍተት ማይሰጥ ቡድን ገንብተዋል። ከባለፉት ጨዋታዎች በብዙ ረገድ ተሻሽለው የቀረቡት ድሬዎች በተለይም በመጀመርያዎቹ 15 ደቂቃዎች አጥቅተው በመጫወት በርከት ያሉ የግብ ዕድሎችን አምክነዋል በተለይም ኢታሞኔ ኬይሙኒ ራምኬል ሎክ በግሩም ሁኔታ ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ ከሰንደይ ሮቴስሚ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ሰንደይ በግሩም ሁኔታ የመለሰለት ኳስ በድሬዎች በኩል እጅግ የሚያስቆጭ ሙከራ ነበር።
እንደባለፈው ጨዋታ ዛሬም በ 3-5-2 አደራደር የገቡት ሽረዎች አጨዋወቱን በሚገባ መላመድ አቅቷቸው ታይተዋል። በተለይም ቡድኑ በመሀል ሜዳ ሚጠቀማቸው ተጫዋቾች ሰለሞን ገ/መድህን ፣ ሄኖክ ካሳሁን፣ ንስሃ ታፈሰ የመከላከል ባህሪ የሌላቸው እና ተመሳሳይ መሆን ተከላካይ ክፍሉ አጋልጦት ነበር። ሽረዎች በመጀመርያው አጋማሽ ዲሜጥሮስ ከመሃል ሜዳ አከባቢ መቶት ለጥቂት ከግቡ በላይ ከወጣችው ኳስ ውጭ ሌላ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። በአንፃሩ ጨዋታው ከተጀመረ ጀምሮ አጥቅተው የተጫወቱት ድሬዎች በርካታ ዕድሎች አምክነዋል። ከነዚህ ውስጥ ከግቡ በቅርበት የተሰጠውን ቅጣት ምት ራምኬል ሞክሮ የግቡ አግዳሚ የመለሰበት እና ራሱ ራምኬል ሎክ የተከላካዮች ስህተት ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ቢገናኝም በጨዋታው ኮከብ ሆኖ ያመሸው ሰንደይ ሮቴሚ በሚያስደንቅ ሁኔታ ግብ ከመሆን ያዳነው የሚጠቀሱ ሙከራዎች ናቸው።
ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ፉክክር የታየበት እና በሁለቱም ቡድኖች በኩል ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታዩበት ነበር። በዚህ አጋማሽ የተሻለ ሆነው የቀረቡት ሽረዎች ሁለቱ የኣማካይ መስመር ተጫዋቾቻቸው በጥልቀት እንዲጫወቱ እና ለተከላካይ ሙሉ ሽፋን እንዲሰጡ ካስቻሉ በኋላ በመሃል ሜዳ ላይ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢያሳዩም በመከላከል ባህሪ ባላቸው ኣማካዮች የተሞላው ጠጣሩ የድሬዳዋ መሀል ክፍል ሰብረው ሙከራ ለማረግ ግን አልታደሉም ለዚ እንደማሳያ ቡድኑ ክፍሎም ማዓሾ ኣክርሮ መቶ ፍሬው ጌታሁን ካዳነበት ሙከራ ውጭ ይህ የሚባል አስደንጋጭ ሙከራ ማድረግ አልቻለም።
ከመጀመርያው አጋማሽ ሲነፃፀር የተቀዛቀዙት ድሬዎች በሁለተኛው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎችን ነበር ያደረጉት። ከነዚህ ውስጥ ወሰኑ ማዜ አክርሮ መቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት እና ሲላ ኣብዱላሂ አክርሮ መቶ ኢላማው ሳይጠብቅ የወጣው ሙከራ ይጠቀሳሉ። በመጨረሻም ጨዋታው በመደበኛው ክፍለ ግዜ ግብ ባለማስተናገዱ ወደ መለያ ምቶች አምርቶ ድሬዳዋ ከተማዎች 4-3 አሸንፈው እሁድ ለሚደረገው የፍፃሜ ጨዋታ ማለፋቸው አረጋግጠዋል።
ቀጥሎ የተደረገው የመቐለ 70 እንደርታ እና ደደቢት ጨዋታ ሙሉ የጨዋታ ብልጫ በነበረው መቐለ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በጨዋታው የመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው መቐለዎች ኳስ ከሜዳቸው መስርተው ለመውጣት ሲሞክሩ በመሀል ሜዳ በነበራቸው የተጠጋጋ የተጫዋቾች ቦታ አያያዝ ምክንያት የኳስ ፍሰቱ ከመሃል ሜዳ እና ከራሳቸው የሜዳ ክልል ሳያልፍ እና ሙከራ ሳያደርጉ ቆይተው ነበር። ብዙም ሳይቆዩ የሁለቱ አማካዮቻቸው ቦታ አያያዝ ከጎንዮሽ ይልቅ የሜዳው ቁመት የተከተለ በማረግ በ10 ቁጥር ሚና የተሰለፈው ሀይደር ሸረፋ ለአጥቂው ያሬድ ከበደ ቀርቦ እንዲጫወት ያረጉት መቐለ 70 እንደርታዎች ከመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በተሻለ የጨዋታ ፍሰት አሳይተዋል።
ዳንኤል ጌድዮን ከግብ ጠባቂው ሶፈንያስ ሰይፈ አንድ ለ አንድ ተገናኝቶ ባመከነው ድንቅ ሙከራ የጀመረው ጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል በመጀመርያዎቹ 30 ደቂቃዎች ያለቀላቸው የግብ እድሎች መክነዋል። በደደቢት በኩል ዓለምባንተ ካሳ ከርቀት ኣክርሮ መቶ ሶፈንያስ ያዳነበት በመቐለ በኩልም አማኑኤል በሁለት አጋጣሚዎች ያመከናቸው ንፁህ የግብ እድሎች ይጠቀሳሉ። በተለይም በጨዋታው ኮከብ ሆኖ የዋለው ያሬድ ከበደ አሻግሮለት ከማታውሲ ፊት ለ ፊት ተገናኝቶ ያመከነው ይጠቀሳል።
ቀሰ በ ቀሰ በተጋጣሚያቸው ሙሉ ብልጫ የተወሰደባቸው ደደቢቶች በመሃል ሜዳ ጥሩ ሲንቀሳቀሱ በነበሩት አቤል እንዳለ እና ዓለምባንተ ካሳ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ቢያገኙም ለግብ የቀረበ ሙከራ አላደረጉም። በ 40 ደቂቃ ላይ ያሬድ ከበደ እና ጋብርኤል መሓመድ በጥሩ ሁኔታ ተቀባብለው ጋብርኤል መሃመድ ከሳጥኑ ውጭ ኣክርሮ መሬት ለ መሬት በመምታት ጎል ኣስቆጥሮ ቡድኑን 1-0 እየመራ ወደ እረፍት እንዲወጣ አስችሏል።
ሁለተኛው ኣጋማሽ ሙሉ በሙሉ የመቐለ 70 እንደርታዎች የበላይነት የታየበት እና ደደቢቶች በተለይም የመጨረሻዎቹ 30 ደቂቃዎች ተዳክመው የታዩበት ነበር። አጋማሹ እንደተጀመረ ሃይደር ሸረፋ ከሳጥኑ ጠርዝ ያገኛትን ኳስ ተጠቅሞ አክርሮ በመምታት የመቐለን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። ጨዋታው ብዙም ያልከበዳቸው መቐለዎች የአማካይ ክፍል ተጫዋቾቻቸው በተጋጣሚ ተከላካይ ክልል ፊት በሚፈጠረው ክፍተት (በደደቢት ተከላካይ እና ኣማካይ ክፍል መሃል) ላይ በብዙ የጨዋታ እንቅስቃሴዎች ወቅት በመገኘትና ጫና በመፍጠራቸው ተጋጣሚ ቡድን አደረጃጀት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳረፍም በላይ የተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮችን ለተሳሳተ ውሳኔዎች የዳረገ ነበር። በ58 ደቂቃ ላይ በአምበሉ ሚኪኤለ ደስታ ጎል አስቆጥረው የጎል መጠናቸው ወደ 3 ከፍ ኣድርገዋል።
በጨዋታው ብልጭ ድርግም የሚል እንቅስቃሴ ያሳዩት ደደቢቶች በአንዳንድ የጨዋታው እንቅስቃሴዎች ማራኪ አጨዋወት እና የአንድ ሁለት ቅብብል ቢያሳዩም እንቅስቃሴው ቀጣይነት አልነበረውም። በዚ ምክንያትም በሁለተኛው ኣጋማሽ የፈጠሯቸው የግብ እድሎች ጥቂት ናቸው። ምስጋናው መኮንን ሶስት ተጫዋቾች ኣታሎ ገብቶ ያልተጠቀመበት እና ሄኖክ መርሹ ከቅጣት ምት መትቶ ወደ ላይ የወጣበት ሙከራዎሽ በደደቢት በኩል ይጠቀሳሉ።
በ66ኛው ደቂቃ ላይ ሃይደር ሸረፋ ያሻማውን ኳስ በመቐለ የሙከራ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው የቀድሞ የናዝሬት ሊሊት አጥቂ ኦሰይ ማውሊ በግንባሩ በመግጨት ግብ አስቆጥሮ ልዩነቱን ወደ አራት ሲያሰፋ በደደቢት በኩል በ83ኛው ደቂቃ ላይ አብዲ መሃመድ ያሻማውን ኳስ አክዌር ቻም በግንባሩ ገጭቶ የደደቢት ብቸኛ ጎል በማስቆጠር ጨዋታው በመቐለ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውድድሩ ፍፃሜውን ሲያገኝ በአንድ ምድብ የነበሩት መቐለ 70 እንደርታ እና ድሬዳዋ ከተማን ያገናኛል።