የከፍተኛ ሊጉ ክለብ ስልጤ ወራቤ አብዱልወኪል አብዱልፈታህን በዋና አሰልጣኝነት ሲሾም ከ20 ዓመታት በላይ በተጫዋችነት በማሳለፍ ኳስን ያቆመውገረሱ ሻመናን ደግሞ በረዳት አሰልጣኝነት ሾሟል፡፡
ባለፈው የውድድር ዓመት ወጣ ገባ አቋም ሲያሳይ የነበረው ስልጤ ወራቤ ዋና አሰልጣኝ የነበረው ኑሩ መሀመድን በማሰናበት በረዳት አሰልጣኝነት ሲሰራ የነበረው ወጣቱ አሰልጣኝ አብዱልወኪል አብዱልፈታህን በዋና አሰልጣኝነት ቀጥሯል፡፡ ከ2005 ጀምሮ የስልጤ ወራቤ ግብ ጠባቂ የነበረው አብዱልወኪል እስከ 2007 ድረስ በክለቡ ሲጫወት ከቆየ በኋላ በጉዳት ምክንያት በወጣትነት እድሜው በመገለል የc ላይሰንስ የአሰልጣኝነት ስልጠናን በመውሰድ ወደ አሰልጣኝነት ሙያ የገባ ሲሆን የስልጤ ዞን ቡድንን በመያዝ በደቡብ ክልል ደረጃ 2009 ላይ ቻምፒዮን ካደረገ በኋላ በ2010 የስልጤ ወራቤ ምክትል አሰልጣኝ በመሆን ሲሰራ ቆይቶ አሁን ደግሞ ገና በ25 ዓመት እድሜው የስልጤ ወራቤ ዋና አሰልጣን ሆኖ ተሹሟል፡፡ ይህም የሊጉ ወጣቱ አሰልጣኝ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአብዱልወኪል ረዳትነት የተሾመው የተሾመው ገረሱ ሻመና ከ1980ዎቹ ጀምሮ በተጫዋችነት ያገለገለ ሲሆን የሊግ ቻምፒዮንነት ክብርን ባሳካበት ሀዋሳ ከተማ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ፖሊስ እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ ከ2006 ጀምሮ እስከ 2010 ድረስ ደግሞ በስልጤ ወራቤ በአምበልነት ሲጫወት ቆይቶ ከእግርኳስ ዓለም በመገለል በወሰደው የአሰልጣኝነት ስልጠና መሠረት በ2011 የስልጤ ወራቤ ምክትል አሰልጣኝ ሆኖ የሚሰራ ይሆናል፡፡