የውድድር ዓመቱ ሊጀመር አንድ ሳምንት ሲቀረው የሚደረገው የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ዘንድሮ በሁለት ቀናት ተራዝሞ ነገ አመሻሽ ላይ ይከናወናል። ተጋጣሚዎቹም የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን ጅማ አባ ጅፋር እና አምና ተጀምሮ ባሳለፍነው ወር የተገባደደው የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ መከላከያ ናቸው።
እንደብዙዎቹ የሀገራችን ክለቦችም ሁለቱ ተጋጣሚዎች በርካታ ዝውውሮችን ፈፅመው እና የአምናውን መልካቸውን በብዙው ቀይረው ነው ነገ የሚገናኙት። ጨዋታውም እንደወትሮው በሊጉ ጅማሮ ዋዜማ ለአሸናፊው ከሚጨምረው በራስ መተማመን ባለፈ የዋንጫ ፍልሚያ እንደመሆኑ መጠን ክለቦቹ ሙሉ ኃይላቸውን የሚጠቀሙበት ብሎም በ2011 ምን ሊመስሉ እንደሚችሉ ጥቆማ የምናገኝበት እንደሚሆን ይታመናል።
ከትናንት በስትያ በአዲስ አበባ ዋንጫ የደረጃ ጨዋታ የተገናኙት ጅማ አባ ጅፋር እና መከላከያ በውድድሩ ዕድል ያላገኙ ተጫዋቾቻቸው ሲጠቀሙ የታየ ቢሆንም የነገው ፍፃሜ ከዛ የተለየ እንደሚሆን ዕሙን ነው። ዘንድሮ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ላይ ተሳታፊ የሆኑት ሁለቱ ክለቦች የአሸናፊዎች አሸናፊ ለመሆን ከቅዳሜው ጨዋታ ከፍ ያለ ፍልሚያ እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።
በ1977 የተጀመረው ይህ ውድድር ከዚህ ቀደም ለውድድሮች መዝጊያነት ሲውል የቆየ ቢሆንም ከ1990ዎቹ መጀመርያ ወዲህ ከአዲሱ የውድድር ዘመን መጀመር በፊት እየተደረገ ይገኛል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 16 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ቀዳሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቡና 5 ፣ ኤሌክትሪክ 3 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ይከተላሉ፡፡