ዘንድሮ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ስሑል ሽረ ወላይታ ድቻን ያስተናገደበት የመጀመሪያ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል። የሁለቱ ክለቦች አሰልጣኞች በተለይም ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
“ተጋጣሚያችን አስቸጋሪ ቡድን አልነበረም ፤ ማሸነፍ ይገባን ነበር” ዳንኤል ፀሀዬ ስሁል ሽረ
” ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ ማሸነፍም ይገባን ነበር። ከመጀመሪያ አጋማሽ እስከ ሁለተኛውም አጋማሽ መሀል ላይ ብልጭ የሚሉ እንቅስቃሴዎች እንጂ በይበልጥ ተጭነናቸዋል። ብዙ የግብ አጋጣሚንም መፍጠር ችለን ነበር ፤ ግን አልተጠቀምንባቸውም። እንደ መጀመሪያ ጨዋታ ግን ጥሩ ነበርን። ለኛ ማሸነፍ የሚገባንም ጨዋታ ነበር። ቡድኔ ኳስ መስርቶ በመጫወት ጥሩ ነበር። ግን በመጀመሪያው አጋማሽ ቶሎ ቶሎ አጥቅተን ጎል ማግባት ሲገባን ትንሽ ተዘናግተን ነበር። ይበልጥ ግን በሁለተኛው አጋማሽ በልጠን መጫወት ችለናል። ድቻዎችም መሀል ላይ አንድ ሁለት ለመጫወት ይሞክራሉ እንጂ ረጃጅም ኳስ ነበር ሚጠቀሙት። ሆኖም ብዙም ተጋጣሚያችን አስቸጋሪ ቡድን አልነበረም ማሸነፍ ይገባን ነበር። ”
“ተመጣጣኝ ጨዋታ ነበር” ዘነበ ፍሰሀ ወላይታ ድቻ
“ጨዋታው ጥሩ ነው ፤ ምንም አይልም። ተመጣጣኝ ጨዋታ ነበር። እነሱም ጥሩ ነበሩ እኛም ጥሩ ነበርን። አልፎ አልፎ ትንሽ እንዳሰብነው አልነበርንም። መቆራረጦች ነበሩ። ለኔ ግን መልካም ነው። የመጀመሪያ ሳምንት እንደመሆኑ መጠን ትንሽ አሁንም በቡድኔ የቅንጅት ችግር አለ። ባለፈው ጥሩ እየመጣን ነበር ዛሬ ግን ትንሽ መቆራረጥ ይታይ ነበር። ይህን ነገር ለማስተካከል ባሉን ጊዜዎች ተጠናክሮ ለመቅረብ እንሰራለን።”