በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ሳምንት የመጀመርያ ጨዋታ ሀዋሳ ላይ ባህር ዳር ከተማን ያስተናገደው ሲዳማ ቡና ነጥብ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ጨዋታውን ፈፅሟል። በመጀመርያው አጋማሽ የተፈጠረ ክስተትም ጨዋታው ለ35 ደቂቃዎች እንዲቋረጥ ምክንያት ሆኗል።
በሁለተኛው ሳምንት ሲዳማ ቡና ከወላይታ ድቻ ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ከ ስሑል ሽረ ጋር ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በተስተካካይነት ተይዞ ወደ ሦስተኛው ሳምንት ያመሩት ሁለቱ ቡድኖች ካለፈ ጨዋታቸው መጠነኛ ለውጥ አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ባለሜዳው ሲዳማ ቡና በሊጉ ጅማሮ አፄዎቹን 2-1 ሲረታ ከተጠቀመበት ቋሚ አሰላለፍ ዳግም ንጉሴን በወንድሜነህ ዋይናለም፣ ጸጋዬ ባልቻን በመሐመድ ናስር በመተካት ወደ መጀመሪያው አሰላለፍ ሲያካትት የጣና ሞገዶች አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ፈረሰኞቹን ሲረቱ የተጠቀሙበትን ሙሉ ስብስብ ተጠቅመው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ቁጥራቸው በርከት ባሉ የሲዳማ ቡናና ረጅም ርቀት አቋርጠው በመጡ የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ደማቅ የድጋፍ ድባብ ታጅቦ በፌዴራል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው መሪነት የተጀመረው ጨዋታ አጀማመር እምብዛም ሳቢ ያልነበረ ሲሆን የረዘው የገቡት አቀራረብ ምን እንደሚመስልም ለመለየት አስቸጋሪ ያደረገ ነበር። በ12ኛው ደቂቃ የግራ ተከላካዩ አስናቀ ሞገስ በረጅሙ የተለጋን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ሳጥን ውስጥ በመግባት ወደ ግብ የሞከራት የመጀመሪዋ ሙከራ ስትሆን 14ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታው የመጀመርያ ጎል ተስተናግዷል። ሐብታሙ ገዛኸኝ ወደ ግብ የመታትን ኳስ ተከላካዩ አቤል ውዱ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ አዲስ ግደይ በምንተስኖት አሎ መረብ ላይ አሳርፎ ሲዳማ ቡናን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
ይህች ግብ ከተቆጠረች በኃላ ግን የጨዋታውን ትኩረት የቀየረ ክስተት ተስተናግዷል። ከውጪኛው የስታዲየሙ ክፍል (በትሪቡኑ ጀርባ) አንድ የፀጥታ አካል ወደ ስታዲየም ለመግባት እየተዘጋጁ ያሉ ደጋፊዎች ላይ የወረወረው የአስለቃሽ ጭስ ወደ ስታዲየሙ በቀጥታ በመግባት በተለይ በትሪቡኑ ባሉ በርካታ ደጋፊዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት ሲያስከትልና የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ተመልክተናል። በዚህም ምክንያት በሜዳ ላይ ሁለቱ ክለቦች ጨዋታቸውን እያደረጉ ሳሉ ዳኛው ሁኔታው እስኪረጋጋ ድረስ ጨዋታውን ለማቋረጥ ተገዷል። ከ10 ደቂቃዎች በኃላ ጨዋታውን ለማስጀመር ዳኛው ቡድኖቹን ወደ ሜዳ ቢጋብዝም የባህር ዳር ተጫዋቾች እና አሰልጣኞች “ተጫዋቾቻችን በመጎዳታቸው አንጫወትም።” በማለት ለተጨማሪ ደቂቃዎች ሳይጀመር ቆይቶ በመጨረሻም ከ35 ደቂቃዎች መቋረጥ በኋላ በድጋሚ ተጀምሯል።
ጨዋታው ዳግም ከተጀመረ በኋላ ባህር ዳሮች ግብ ለማስቆጠር በሁለት አጋጣሚዎች የፈጠሯቸው ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ተጠቃሽ ሲሆኑ በተለይ ዳንኤል ከግብ ጠባቂው መሣይ ጋር ተገናኝቶ መሣይ ያስጣለው ይጠቀሳል። በሲዳማ በኩል ደግሞ ሐብታሙ ገዛኸኝ ያመከናት መልካም አጋጣሚ የምትጠቀስ ነበረች።
በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች ለውጥን ያደረጉት ሁለቱ ክለቦች ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴን ማድረግ ችለዋል። አጋማሹ እንደተጀመረ 48ኛው ደቂቃ ላይ ግርማ ዲሳሳ ወደ ሲዳማ የግብ ክልል አክርሮ የመታትን ኳስ ግርማ በቀለ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት በጨዋታው ድንቅ የነበረው ዳንኤል ኃይሉ አስቆጥሮ ባህር ዳርን አቻ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ በኃላ ሲዳማዎች በድጋሚ ወደ መሪነት ለመመለስ ጥረት አድርገዋል። ወደ ባህር ዳር የግብ ክልል በጥሩ ቅብብል በመድረስ ሐብታሙ ገዛኸኝ ሞክሮ የግብ ቋሚ ብረት የመለሰበህ እንዲሁም 78ኛው ደቂቃ ላይ ጸጋዬ ባልቻ ያገኛትን መልካም አጋጣሚ ምንተስኖት አሎ ያዳነበትም ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ናቸው። በ81ኛው ደቂቃ ላይ የጣና ሞገደኞቹ አሸናፊ ለመሆን የተቃረቡበት የግብ እድል መፍጠር ችለው ነበር። ጋናዊው አጥቂ አህመድ ዋታራ ላይ የሲዳማ ቡናው ግብ ጠባቂ መሣይ አያኖ ጥፋት በመፈፀሙ ምክንያት በድጋሚ ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ዳንኤል ኃይሉ ቢያስቆጥርም ከዳኛው ፊሽካ በፊት ተጫዋቾት ወደ ሳጥን በመግባታቸው በድጋሚ መትቶ መሣይ አያኖ አድኖበታል።
በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ከሁለቱም በኩል አሸናፊ የሚያደርጋቸውን ግብ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ሲዳማ ከሁለት የሜዳው ጨዋታዎች አራት ነጥብ ሲያሳካ ባህር ዳር ከተማም በመጀመርያ የሊግ ተሳትፎው ከሁለት ጨዋታ በተመሳሳይ አራት ነጥብ መያዝ ችሏል።
ጨዋታውን የመራው ፌዴራል ዳኛ ተፈሪ አለባቸው ዘጠኝ የማስጠንቀቂያ ካርዶች እና ሦስት ፍፁም ቅጣት ምቶች ሰጥተዋል። እነዚህ እና ሌሎች መረጃዎችን ከታች ያለውን ሊንክ ተጭነው ያገኛሉ፡-
የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ሊንኩን ተጭነው ያገኛሉ: LINK |