ደቡብ ፖሊስ ከ ደደቢት – ቅድመ ዳሰሳ 

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከ18 ቀናት መቋረጥ በኋላ ዛሬ በተደረገ አንድ ጨዋታ ሲጀምር በነገው ዕለትም ሀዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስ ከ ደደቢት በሚያደርጉት ጨዋታ ይቀጥላል። የውድድር ዓመቱ ከተጀመረ ወዲህ ነጥብ ማስመዝገብ ያልቻሉት ክለቦቹ በዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ነጥብ ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።
በርከት ያሉ በሊጉ የረጅም ዓመት ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በማስፈረም ሊጉን የጀመረው ደቡብ ፖሊስ በመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ በሜዳው መከላከያን ገጥሞ መሸነፉን ተከትሎ በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ላለመጣል ከባለፈው ጨዋታ በተሻለ አጥቅቶ ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል። 

ከተጋጣሚው ደቡብ ፖሊስ በተቃራኒው የሊጉ ልምድ የሌላቸው ወጣት ተጫዋቾች በመያዝ ዓመቱን የጀመረው ደደቢትም በተመሳሳይ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በመቐለ እና ኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት በማስተናገዱ ባለፉት ጨዋታዎች ላይ ከነበረው ክፍት አጨዋወቱ በተለየ የጨዋታ አቀራረብ ይዞ ሊገባ እንደሚችል ይገመታል። በፋይናንስ ችግር ላይ የሚገኘው ክለቡ ይህ ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲሸጋገርለት ቢጠይቅም ምላሽ ባለማግኘቱ ነገ በተያዘለት መርሐ ግብር መሰረት እንደሚካሄድ ይጠበቃል። 

በጨዋታው ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል የደደቢት ሊጉን የመቋቋም አቅም አንዱ ነው። ቡድኑ በተከታታይ ከመሸነፉ በተጨማሪ ከሜዳው ውጪ ለመጀመርያ ጊዜ ጨዋታ የሚያደርግ ከመሆኑ አንጻር ልምድ አልባው ስብስብ በምን መልኩ የመጀመርያ የሜዳ ውጪ ጨዋታውን ይወጣዋል የሚለው የሚጠበቅ ይሆናል። የደቡብ ፖሊስ ስብስብም እንዲሁ በበርካታ አዳዲስ ተጫዋቾች የተገነባ ከመሆኑ አንጻር ምን ያህል ተዋህዷል የሚለውን ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፍንጭ የሚሰጥበት ጨዋታ እንደሚሆን ይጠበቃል። 

ከጨዋታው ጋር በተያያዘ የቡድን ዜና በደቡብ ፖሊስ በኩል አዲስ ፈራሚው ዘነበ ከድር የማይሰለፍ ሲሆን በደደቢት በኩል የተጎዳ ተጫዋች የለም። በሁለተኛው ሳምንት ወደ 23 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በማቅናታቸው ምክንያት ያልተሰለፉት የዓብስራ ተስፋዬ እና አቤል እንዳለ ወደ ቡድኑ ስብስብ በመመለሳቸው እንዲሁም ጋናዊው ግብ ጠባቂ ረሺድ ማታውሲ የስራ ፍቃድ በማግኘቱ ይሰለፋል ተብሎ ይጠበቃል።

የእርስ በርስ ግንኙነት 

ሁለቱም ክለቦች በሊጉ ከ8 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ይገናኛሉ። ለደቡብ ፖሊስ (ዘንድሮ ከማደጉ በፊት) የመጨረሻው፣ ለደደቢት ደግሞ የመጀመርያው የሊግ ዓመት በነበረው 2002 ተገናኝተው በመጀመርያ ዙር አዲስ አበባ ላይ ደደቢት 3-0 ሲያሸንፍ በሁለተኛው ዙርም ሀዋሳ ላይ 2-0 ድል የቀናው ደደቢት ነበር። 

ዳኛ 

ጨዋታው በፌዴራል ዳኛ ሐብታሙ መንግስቴ ይመራል። ሐብታሙ በዘንድሮወ የውድድር ዓመት የመጀመርያ ጨዋታውን የሚመራ ይሆናል። 

ግምታዊ አሰላለፍ

ደደቢት (4-2-3-1)

ረሺድ ማታውሲ

ኄኖክ መርሹ – ኤፍሬም ጌታቸው – ክዌክ አንዶህ – መድሃኔ ብርሃነ

ኩማ ደምሴ – ያብስራ ተስፋዬ

አቤል እንዳለ – አለምባንተ ካሳ – ያሬድ መሐመድ

አሌክሳንደር ዓወት

ደቡብ ፖሊስ (4-4-2)

ዳዊት አሰፋ

ብርሀኑ በቀለ – ሳምሶን ሙሉጌታ – ደስታ ጊቻሞ – አበባው ቡጣቆ 

መስፍን ኪዳኔ – አዲስዓለም ደበበ – ሙሉዓለም ረጋሳ – ብሩክ ኤልያስ 

የተሻ ግዛው – በረከት ይስሀቅ