የአሰልጣኞች አስተያየት | ሲዳማ ቡና 1-1 ባህር ዳር ከተማ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ዛሬ መካሄድ ሲጀምር ሀዋሳ ላይ በሲዳማ ቡና እና ባህር ዳር ከተማ መካከል የተከናወነው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞችም በጨዋታው ዙርያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 
“ጨዋታው በመሀል መቋረጡ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል” ዘርዓይ ሙሉ (ሲዳማ ቡና)

ስለ ጨዋታው 

ጨዋታው ለእኔ ሶስት አይነት ነበር። ስንጀምር የነበረው የአጨዋወት መንገዳችን የተሳካ ነበር፤ እየመራንም ነበር። ጨዋታው በመሀል መቋረጡ ደግሞ ሌላ ተፅዕኖ ፈጥሯል። ምክንያቱም በዛ ሰዓት እያጠቃን ስለነበር ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር እንችል ነበር። ከተቋረጠ በኃላ ግን ቡድናችን መስተካከል አልቻልንም። ከዛ ውጭ የመጀመርያው አጋማሽ የተመጣጠነ ነበር። ከእረፍት በኃላ ግን በተለይ ወደ ብሔራዊ ቡድን የሄዱ አምስት ተጫቸቾቻችን አቅም ጨርሰዋል።  መሀል ክፍላችንም ጥሩ አልነበረም። እዚህ ላይ እንሰራለን እናስተካክላለን። ብልጫውን የወሰዱብን መሀል ላይ ነው፤ ያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት ይዘው ይሄዳሉ። ተደጋጋሚ ጫናዎች የበዙብንም መሀል ላይ ኳሶች ይቆረጡ እና ይበላሹ ስለነበር ነው።

ሰለ አጨዋወት 

ተቃራኒ ቡድን ይዞት የመጣው አጨዋወት ወደ መስመር ወጥተን እንድንጫወት አስገድዶናል። መሀሉን ዘግተው ስለሚጫወቱ ያለን የመጫወቻ ስፍራም በመስመር ስለሆነ ነው በተደጋጋሚ ወደዛ አድልተን ስንጫወት የነበረው። ለዛ ነው የፊት አጥቂዎቻችን ኳስ የማያገኙት። 

የአጨራረስ ድክመት

አምስት ተጫዋቾች ብሔራዊ ቡድን አሰመርጠን ነበር። እነዚህ ተጫዋቾች ምንም የቅንጅት ስራ መስራት አልቻሉም። ይህ ደግሞ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል። አንድ ሁለት ቀን ቢኖረን ኖሮ ክፍተቶቻችን ላይ እንሰራ ነበር። ከዚህ በኃላ ሰፊ ጊዜ ስላለ እዚህም ላይ ሰርተን እንመጣለን።

” በዳኛው ውሳኔ ቅር አልተሰኘሁም” ጳውሎስ ጌታቸው (ባህር ዳር ከተማ)

ስለጨዋታው

ጨዋታ ላይ አንዳንድ ክስተቶች አይፈጠሩም ማለት አይቻልም። ምክንያቱም ኳስ ጨዋታ ነው። ዛሬ የሲዳማም ሆነ የሀዋሳ ህዝብ ኳስ እንደሚወድ ያየሁበት፤ ዘጠና ደቂቃ ቡድኑን ሲደግፍ ስለነበር ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ። ምክንያቱም ጨዋታውም አልቆ ከቡድናቸው ጋር ነው ያሉት። ጨዋታው እንዳያችሁት እልህ እና ኃይል የነበረው ነው። የመጀመሪያው 15 እና 20 ደቂቃ በጣም ብልጫ ተወስዶብን ነበር። ነገር ግን ከዛ በኃላ ብልጫ ወሰድን፤ ብዙ ኳሶች ማግባት ነበረብን። ጨዋታውን ከእረፍት በፊት እንጨርሳለን በሚል ግምትም ነበረኝ፤ ምክንያቱም ጎል ጋር ቶሎ ቶሎ በክንፍ ላይ እንደርስ ነበር።

ከእረፍት በኋላ እኛ አጥቅተን መጫወት ነበረብን። ፍፁም ቅጣት ምት አገባን፤ የሚቀጥለውንም ፍ/ቅጣት ምት አገኘን፤ አገባን። ድጋሚ ይመታ ተብሎ ሳትን። ይህ የዳኛው ውሳኔ ስለነበር በዚህ ምንም ቅር አላለኝም። ተሽሮ 1 ለ 1 ወጥተናል። ይሄን ውጤት ይዤ ለመሄድ ጠብቄ ነበር አሳክቼዋለሁ። 

የተጫዋቾች ያለመሟላት

ለኔ ማንም ኮከብ ተጫዋች የለም። ለምሳሌ ጃኮ አራፋት ነገ ወረቀቱ ቢያልቅበት ነገ ይሄን ሜዳ አያየውም፤ ብዙ መስራት ይጠበቅበታል። ያሉትን ተጫዋቾች አይታችዋል። ስለዚህ እኔ በዛ ላይ እጠነቀቃለሁ። ጥሩ ነገር አንድ ሶስት ተጫዋቾች ከአፍሪካ አካትቻለሁ። ያን ያደረኩት ተጫዋቾቹ እንዲነሳሱልን ነው እንጂ ሌላ ታሪክ የለውም። ለኔ ሁሉም አንድ ናቸው። 

ስለጨዋታው መቋረጥ

የጨዋታው መቋረጥ አዲስ አየረደለም፤ የትም ይፈጠራል። ጭሱ ሆን ተብሎ የተደረገ ነገር ስላልሆነ እንደኳስ ክስተት ነው የማየው። ምንም ነገር የተለየ ነገር አላየሁም።