የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ዛሬ በሁለት ጨዋታዎች ሲቀጥል ሽረ ላይ ስሑል ሽረ ከአዳማ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ባለሜዳው ስሑል ሽረ በመጀመርያው ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር በተደረገው ጨዋታ ከነበረው ስብስብ በደሳለኝ ደበሽ፣ ጅላሎ ሻፊ እና ሰዒድ ሁሴን ምትክ ሸዊት ዮሀንስ፣ ሰለሞን ገብረመድህን እና ሚዲ ፎፋናን ሲጠቀሙ አዳማ ከተማ ደግሞ ሮበርት ኦዶንካራ፣ አንዳርጋቸው ይላቅ፣ ሙሉቀን ታሪኩ፣ ቴዎድሮስ በቀለ እና ዐመለ ሚልኪያስን በጅማ አባጅፋር ከተሸነፈው ስብስብ ለውጥ ተደርጎ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ የተካተቱ ተጫዋቾች ናቸው።
የስሑል ሽረ ቡድን አመራሮች ለአዳማ ከተማ የሽረ ምስል ያለበት ፎቶ በስጦታ በማበርከት በተጀመረው ጨዋታ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በሁለቱም በኩል ታይቷል። በ17ኛው ደቂቃ ላይ የስሑል ሽረ ተከላካይ ዘላለም በፈጠረው ስህተት አማካኝነት የተገኘውን ኳስ ዳዋ ሁቴሳ ደርሶበት በቀጥታ ወደ ግብ ቢመታውም ግብ ጠባቂው ሰንደይ ሮትሚ እንደምንም ወደ ውጭ ያወጣበት የጨዋታው የመጀመርያ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። በ19ኛው ደቂቃ ላይ ኢብራሂም ሚዶና ከርቀት የሞከረውና በሮበርት በቀላሉ የተያዘበት ደግሞ በሽረ በኩል የመጀመርያ ሙከራ ነበር።
አዳማዎች መሐል ሜዳን በሚገባ በመቆጣጠር በተሻለ ሁኔታ ጫን ብለው የተጫወቱ ሲሆን በ25ኛው ደቂቃ ላይ አንዳርጋቸው ይላቅ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት ከአግዳሚው በላይ ሊወጣበት ችሏል። በ32ኛው ደቂቃ ስሑል ሽረዎች በጥሩ ቅብብል ወደ አዳማ ከተማ የግብ ክልል ቢደርሱም በተከላከዮች ሲመለስ በመልሶ ማጥቃት ወደ ሽረ የግብ ክልል በመቅረብ ሙሉቀን ታሪኩ ወደግብ አክርሮ የመታው ኳስ አግዳሚው መልሶበታል። ይሄም ከእረፍት በፊት አዳማ ከተማ ያገኘው አስቆጪ የግብ ኣጋጣሚ ሆኗል። የመጀመርያው ምእራፍም ከባድ የሚባሉ ተደጋጋሚ የተጫዋቾች ንክኪ እና በበርካታ ፊሽካዎች ምክንያት ጨዋታው በመጠኑም ቢሆን ተቀዛቅዞ ነበር የተጠናቀቀው።
ከእረፍት መልስ በተመሳሳይ የተሻለ የነበሩት እንግዶቹ አዳማ ከተማዎች ነበሩ። በ74ኛው ደቂቃ ላይ ከመሐል የተሻማውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ሱራፌል ዳንኤል አግኝቶት ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት ሲቀር ተቀይሮ በገባው ጅላሎ ሻፊ ላይ በተሰራ ጥፋት ስሑል ሽረ የቅጣት ምት አግኝተው ሸዊት ዮሃንስ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቢመታውም ግብ ጠባቂው እንደምንም ሊያድንበት ችሏል። ጨዋታው ወደ መጠናቀቁ አካባቢ በጥሩ ቅብብል አዳማ ከተማ በከነዓን ማርክነህ የግብ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው አድኖበታል። ጨዋታውም ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።
ውጤቱን ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች በሁለት ጨዋታ ምንም ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ሲቀሩ ሽረ ሁለት ነጥቦች፣ አዳማ ከተማ ደግሞ አንድ ነጥብ መያዝ ችለዋል።
የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ሊንኩን በመጫን ያገኛሉ |