ትላንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 13 ጨዋታዎች ሲደረጉ በመካከለኛ እና ደቡብ ምስራቅ ምድብ ዲላ ላይ ዲላ ከተማን ከ ወላይታ ሶዶ ከተማ ጋር ያገናኘው ጨዋታ ያለ ግብ በአቻ ውጤት ቢጠናቀቅም በኢትዮጵያ እግርኳስ ባልተለመደ መልኩ የፀደቀ ግብ በአሰልጣኝ ጥቆማ አማካኝነት ተሽሯል።
ጨዋታው እየተደረገ በ62ኛው ደቂቃ ላይ ዲላ ከተማዎች በቀኝ የወላይታ ሶዶ ማዕዘን ጠርዝ ላይ ያገኙት የቅጣት ምት ሲሻማ የዲላ ከተማው የመሐል ተከላካይ ዝናው ዘላለም በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብ ይልካታል። የዕለቱ ፌድራል ዳኛ አፈወርቅ አድማሱም ከረዳቱ ጋር በመነጋገር ግቧን ያፀድቁታል። በዚህም ሂደት የዲላ ቡድን ተጫዋቾች ደስታቸውን ይገልፃሉ። ሆኖም ተጫዋቹ በግምባሩ የገጫት ኳስ ከመረብ ያረፈች ብትመስልም መረቡ የተቀደደ በመሆኑ ከጀርባ በኩል የመረቡን ማሰርያ ገመድ መትቶ ሾልኮ የገባ መሆኑን የግብ አስቆጣሪው ዲላ ከተማ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በማረጋገጣቸው ወደ አራተኛ ዳኛው አብርሃም ኮይራ በመጠጋት ኳሷ ግብ እንዳልሆነች ገልፀዋል። በዚህ ሁኔታ ግራ የተጋቡት የእለቱ ኮሚሽነር ዳኞቹን በመጥራት ካወያዩ በኃላ በስተመጨረሻም የአሰልጣኙን ጥቆማ በመቀበል ግቧ ተሽራ በመልስ ምት እንጂመር ሆኖ ጨዋታው 0-0 በሆነ ውጤት እንዲጠናቀቅ ሆኗል። የዲላው አሰልጣኝ ገብረክርስቶስም በድርጊታቸው ቡድናቸው ሁለት ነጥብ ቢያጣም ትልቅ ክብር የሚያስገኝ ተግባር ፈፅመዋል።
የጉዳዩ ባለቤት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ስለ ክስተቱ አስረድተዋል። “ኳሱ ይሻማል፤ ከተሻማ በኋላ የመረቡን ማሰርያ ገጭታ በጀርባ ቀዳዳ በኩል ትገባለች። ዳኛው እና ረዳቱ በጋራ ሆነው ግቧን ያፀድቋታል። ኳሱም መሀል ሜዳ ላይ መጥታ ልትፀድቅ ስትል ጭቅጭቅ ይነሳና ዳኛውን ይከቡታል። በዚህ መሀል እኔ ደግሞ ዞሬ ስለነበር ከጎሉ ጀርባ ለመግባት ሲያሟሙቅ የነበረን ተጫዋች ስጠይቀው ኳሱ የገባው ከጀርባ ነው ይለኛል። ይህን ልክ እንዳወቅኩ ወደ አራተኛው ዳኛ ጋር ሄጄ ጎል አይደለም ዳኛውን ጥራው አልኩት። ኮሚሽነሩም መጡ፤ ዳኛውን ጥሩትና ጎል እንዳልሆነ ንገሩት አልኩኝ። ዳኞቹም ከተነጋገሩ በኃላ ጎሉ ሳይፀድቅ በመልስ ምት እንዲጀመር አድርጓል።” ብለዋል።
አሰልጣኙ አክለውም “እግር ኳስ ፍትሀዊነትን ይፈልጋል። ለምን VAR ተጀመረ? ስህተት ለመቀነስ አይደለም? ታዲያ እኛ ለምን እንክዳለን? ሲቀጥል ደግሞ ነገ ይህ ጉዳይ እኔ ላይ ቢከሰትና ብንሸነፍስ ብዬ አሰብኩ። ስለዚህ ፍትሀዊ አደለም፤ በፍትሀዊነት ነው ኳስን ማሸነፍ የሚቻለው የሚል ከድሮም ጀምሮ በውስጤ ስላለ ያደረኩት ነው። ይህ ደግሞ የመጀመሪያዬ አይደለም። ከድሮም ጀምሮ የማምነው በፍትሀዊነት ማሸነፍ ነው። ተጫዋቾቼም ይህን እንዲያምኑ ነው የምሰራው። ጎል ብለው ሲጨፍሩ ነበር፤ ሲሻርም ደግሞ ምንም አይነት የፈጠሩት ክርክርም አልነበረም።” በማለት ተናግረዋል፡፡
የተጋጣሚው ሶዶ ከተማ አሰልጣኝ ሐብተየሱስ ጳውሎስ ደግሞ በዕለቱ ስለነበረው ክስተት እንዲህ ያስረዳሉ። “በጨዋታው አጨቃጫቂ ነገር አጋጥሞናል። ኳሱ ከመረቡ ጀርባ ነው የተገኘው። ኳሱን የመታው ልጅ ራሱ ይዞ በሚሄድበት ወቅት ነው ዳኛው ጎል ብሎ ያፀደቀው። ከመሀል ዳኛው በተጨማሪ የረዳት ዳኛውም ውሳኔ ጎል ነው በማለት ነበር የወሰኑት። በዚህ መሐል ዳኛውን ከበው ተጫዋቹቹ በማናገር ሳሉ ነው ኮሚሽነሩ እና ገብሬ እውነታው ኳሱ የገባው ከመረቡ ጀርባ መሆኑን በመግልፅ ጨዋታው በመልስ ምት እንዲጀመር ያደረጉት። ” ብለዋል።
አሰልጣኝ ሐብተየሱስ በድርጊቱ ትምህርት እንዳገኙም ይናገራሉ። ” እውነት ለመናገር በኢትዮጽያ እግር ኳስ ላይ ሁሉም አሰልጣኞች ውጤት ይፈልጋሉ። ገብሬ ያደረገው ለሁላችንም ትልቅ ትምህርት ነው፤ በውሸት ወይም ባልተገባ መንገድ ውጤት ማግኘት እንደማይገባ ከቃል አልፎ በተግባር አሳይቶናል። ገብሬ እውነቱን ከመናገሩ በተጨማሪ የእኛን አመራሮች በማረጋጋት ትልቅ ነገር መስራቱን መናገር እችላለሁ። ለዚህም ለገብሬ ምስጋና ይገባዋል። ገብረክርስቶስ ያደረገው ተግባር ለሁሉም የኢትዮጵያ እግርኳስ ቡድኖች በሀቀኝነት በመስራት በእግርኳስ ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠር እንደሚቻል የሚሳይ ነው። ገብሬ ትልቅ እና ለእውነት የቆመ ሰው ነው። በዚሁ አጋጣሚ የዲላ ደጋፊዎችም የሚመሰገኑ ናቸው። ለምን ጎሉ አልፀደቀም ብለው ብጥብጥ አልፈጠሩም። ጨዋ ደጋፊዎች ናቸው። ዳኞችም ለውሳኔ አለመቸኮል እና ለውሳኔቸው በጣም መጠንቀቅ አለባቸው። የግብ መረብ ለደንቡ ሳይሆን መፈተሽ ያለባቸው በደንብ መፈተሽ አለባቸው።” ሲሉ አስተያየታቸውን አጠቃለዋል።
አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በተጫዋችነትና እና በአሁኑ ሰዓት ደግሞ በአሰልጣኝነት ህይወት ውስጥ ይገኛሉ። ከ1970ወቹ አንስቶ በተለይ በዲላ ከተማ የተጫዋችነት ዘመናቸውን ያሳለፉ ሲሆን ለደቡብ ክልል እንዲሁም በቀድሞ አጠራር ለሲዳማ ክፍል ሀገር በአማካይ ስፍራ ላይ በአምበልነትም ጭምር የእግር ኳስ ህይወትን ያሳለፉ ናቸው። ከዘጠናዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ደግሞ ወደ አሰልጣኝነት ሙያ ውስጥ በመግባት በተለይ በታዳጊዎች ላይ ስራቸውን ጀምረዋል። ለረጅም ዓመታት ከአንደኛ ሊግ አንስቶ እስከ አሁኑ የከፍተኛ ሊግ ውድድር ድረስ በዲላ ከተማ የዋና አሰልጣኝነት መንበር ላይ ይገኛሉ። ከአንድ አመት በፊት ክለቡን ካልመሩበት ጊዜ ውጭ በርካታውን የአሰልጣኝነት ህይወታቸውን በዚሁ የትውልድ ቦታቸው ክለብ በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ። የአሁኖቹ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ጌታነህ ከበደ እና አስቻለው ታመነን ጨምሮ ስመጥር ተጫዋቾችን ለኢትዮጵያ እግር ኳስም አበርክተዋል። በ2004 የስፖርት ኮቺንግ የማስተርስ ባለቤቱ አሰልጣኝ ገብረየስ “በእግር ኳስ የማጥቃት መንገድ” የተሰኘን መፅሀፍን አሳትመው ለንባብ አብቅተዋል። አሁን ደግሞ ለእግርኳሳችን ሌላው ራስ ምታት የሆነውና እንደ ትክክለኛ ነገር የተቀበልነው የሚመስለው ውጤትን ባልገባ መንገድ የማግኘት ባህላችንን ቆም ብለን እንድንጠይቅ የሚያደርግ መልካም ተግባር ፈፅመዋል።