ትላንት መካሄድ የጀመረው የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ መርሐ ግብር ዛሬም በአምስት ጨዋታዎች ቀጥሎ ኢኮስኮ የሳምንቱን ከፍተኛ ድል ሲያስመዘግብ ነጌሌ አርሲ እና ወልቂጤ ከተማ ከሜዳቸው ውጪ ድል አስመዝግበዋል። ሀምበሪቾም ሶስት ነጥብ ከሰበሰቡት መካከል ሆኗል።
በመጀመሪያው ሳምንት በክፍያ መዘግየት ምክንያት ጨዋታውን ያላደረገው የካ ክፍላ ከተማ ኦሜድላ ሜዳ ላይ በ08:00 ነጌሌ አርሲን ገጥሞ 1-0 ሽንፈት ገጥሞታል። የመጀመሪያውን የግብ ሙከራ የየካው ዮናስ ሰለሞን በ23 ኛው ደቂቃ ሲያደርግ በነገሌ አርሲ በኩል ቴዎድሮስ ታምሩ በግንባሩ የገጨውን ኳስ ግብ ጠባቂው ፈድሉ በድሉ ጥረት ታክሎበት ከሽፏል። በ30ኛው ደቂቃ ምትኩ ጌታቸው ከግቡ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ በድጋሚ ግብ ጠባቂው ቀድሞ በመውጣት ሲያድነው በ39 ደቂቃ ግን የጨዋታውን ብቸኛ ጎል መሬት ለመሬት አክሮ በመምታት አስቆጥሯል።
ከዕረፍት መልስ የአቻነት ግብ ፍለጋ በሁለቱም መስመሮች በመጫወት ጫና የፈጠሩት የካዎች በዮናስ ሠለሞን እና ብሩክ ብርሃኑ ያደረጉት የግብ ሙከራ የግቡ አግዳሚ መልሶባቸዋል። ተጋጣሚያቸው ነገሌ አርሲ በተደጋጋሚ በመውደቅ ምክንያት ጨዋታው ቶሎ ቶሎ ሲቆራረጥ ተስተውሏል። በዚህም ምክንያት በ74ኛው ደቂቃ የነገሌው አርሲ ተጫዋች አታሎ በመውደቁ ምክንያት በሁለት ቢጫ ከሜዳ ሲወገድ የቡድኑ ወጌሻ ከሜዳ ውጭ እንዲሆኑ የእለቱ ዳኛ በመወሰናቸው ቀሪውን ጊዜ የጠብታ እምቡላንስ ባለሙያዎች እና የየካ ቡድን ወጌሻ በመግባት ህክምና ሲያደርጉ ተስተውሏል። ከሜዳቸው ውጪ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት የቻሉት ነጌሌ አርሲዎች በምድቡ ሠንጠረዥ ላይ በአራተኛ ደረጃ መያዝ ችለዋል።
መድን ሜዳ ላይ ኢኮስኮ ናሽናል ሴሜንትን አስተናግዶ 4-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ዳንኤል ታደሰ፣ አበበ ታደሰ፣ አቤኔዘር አቶ እና ኢሳይያስ ታደሰ የኢኮስኮን ግቦችን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው። በድሉ ተጠቅሞ ኢኮስኮ የማዕከላዊ እና ምስራቅ ምድብን ኢኮስኮ በነጥብ ከሀምበሪቾ ጋር እኩል በመሆን በ4 የግብ ልዩነቶች አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሀምበሪቾ ዱራሜ ኢትዮጽያ መድንን አስተናግዶ በ55ኛው ደቂቃ ወንድሜነህ ዘሪሁን ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ 1-0 ሲያሸንፍ ወደ ያያ ቪሌጅ በማቅናት የዓመቱ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ወልቂጤ ከተማ መሐመድ ዓሊ በ36ኛው ደቂቃ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ አዲስ አበባ ከተማን 1-0 ማሸነፍ ችሏል። ሀላባ ከተማ ከዲላ ከተማ ያለምንም ግብ ሲለያዩ ቅዳሜ ዕለት በተደረገ አንድ ጨዋታ ወላይታ ሶዶ ከተማ ከድሬዳዋ ፖሊስ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል።