በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ 3ኛ ጨዋታ አዲስ አበባ ስታድየም ላይ የማሊ አቻውን ያስተናገደው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 2-0 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ወደ ሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋውን አጨልሟል፡፡
አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ባለፉት 2 የማጣርያ ጨዋታዎች በቋሚነት ካሰለፏቸው ተጫዋቾች መካከል ሲሳይ ባንጫን በጀማል ጣሰው ፣ ዋሊድ አታን በቶክ ጄምስ ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስን በአሉላ ግርማ ፣ አንዳርጋቸው ይላቅን በታደለ መንገሻ ፣ ዩሱፍ ሳሌህን በአዳነ ግርማ እንዲሁም ጌታን ከበደን በሳላዲን አሲድ ምትክ በቋሚ 11 ውስጥ አካተው ፣ አበባው ቡታቆን ደግሞ አምበል አድርገው ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡
የማሊ የመጀመርያ ግብ የተገኘችው በ32ኛው ደቂቃ ሲሆን ከቅጣት ምት የተሸገረውን ኳስ አብዱላሂ ዲያቢ በጭንቅላት ገጭቶ አስቆጥሯል፡፡ ሁለተኛዋን ግብ ደግሞ በ62ኛው ደቂቃ ሳምቦ ያትባሬ ከቀኝ መስመር የታጠፈለትን ኳስ ተጠቅሞ አስቆጥሯል፡፡
ምድቡን ዛሬ ከሜዳዋ ውጪ ማላዊን 2-0 ያሸነፈችው አልጄርያ ከ3 ጨዋታዎች ሙሉ 9 ነጥብ ሰብስባ ስትመራ ማሊ በ6 ፣ ማላዊ በ3 ፣ ኢትዮጵያ ካለምንም ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
የምድቡ ቀጣይ ጨዋታዎች በቀጣይ ረቡእ ሲካሄዱ አልጀርስ ላይ አልጄርያ ማላዊን ፣ ባማኮ ላይ ማሊ ኢትዮጵያን ያስተናግዳሉ፡፡