ሴቶች 1ኛ ዲቪዝዮን | አዳማ ከተማ ተከታታይ ድሉን ሲያስመዘግብ ጌዴኦ ዲላ ከሜዳው ውጪ አሸንፏል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን አራተኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ በአራት ጨዋታዎች ተጀምሯል። በክልል ከተሞች በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎችም አዳማ ከተማ በሜዳው ሲያሸንፍ ጌዴኦ ዲላ ከሜዳ ውጪ በውጤታማነቱ ቀጥሏል።

አዳማ ከተማ 2-1 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

(በዳንኤል መስፍን)

በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አዳማ ከተማን ከኢትዮ ኤሌትሪክ ያገናኘው ጨዋታ በአዳማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በፈጣን እንቅስቃሴ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ባለሜዳዎቹ አዳማዎች በተደጋጋሚ በፊት አጥቂዎቻቸው አማካኝነት የሚፈጥሩት ጫና ተሳክቶላቸው ገና በ9ኛው ደቂቃ ነበር ሴናፍ ዋቁማ ከመሐል ሜዳ ሰናይት ቦጋለ የጣለችላትን ኳስ ወደ ፊት ገፍታ በመግባት ወደ ጎልነት በመቀየር ቡድኗን መሪ ማድረግ የቻለችው። ኤሌክትሪኮች ጎል ቢቆጠርባቸውም ኳሱን ተቆጣጥሮ በመጫወት ረገድ የተሻሉ ነበሩ ሆኖም የጎል አጋጣሚ ከመፍጠር አኳያ ደክመው ታይተዋል። በመጀመርያው አጋማሽ ተጠቃሽ የጎል ሙከራቸውም ከሳጥን ውጭ የተገኘውን ቅጣት ምት ወርቅነሽ መልመላ መትታ ግብ ጠባቂዋ እምወድሽ አድናዋለች።

ጨዋታው በጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ተጋግሎ ቀጥሎ ባለሜዳዎች አዳማዎች በመልሶ ማጥቃት የሚፈጥሩት የመጥቃት መንገዳቸው ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ተከላካዮች ፈታች የነበረ ሲሆን በተለይ አጥቂዎቹ ሴናፍ ፣ ጤናዬ እና ሰርካዲስ ከአማካኞቹ የሚቀበሉትን ኳሶች ከአንዴም ሁለቴ የማግባት አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀሩ እንጂ ከዚህ በላይ ጎል ማስቆጠር በቻሉ ነበር።

ከእረፍት መልስ የበላይነት የወሰዱት ኢትዮ ኤሌትሪኮች ጫና ፈጥረው ጎል ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ በ56ኛው ደቂቃ ላይ በእለቱ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ሰሚራ ከማል የግቡ ቋሚ የመለሰባት አጋጣሚ የምታስቆጭ ነበረች። የኤሌክትሪክ እንስቶች ጎል ለማስቆጠር እና ወደ ጨዋታው ለመመለስ በከፍተኛ ፍላጎት ተጭነው እየተጫወቱ ባለበት ቅፅበት በ65ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂዋ እስራኤል ከተማ የሰራችውን ስህተት ተከትሎ ነፃ ኳስ ያገኘችው አጥቂዋ ሴናፍ ዋቁማ ለራሷ እና ለቡድኗ አዳማ ሁለተኛ ጎል ስታስቆጥር የውድድር ዓመቱም ሦስተኛ ጎሏ ሆኖ ተመዝግቦላታል።

የጎሉ መቆጠር ከተወሰደባቸው ብልጫ አዳማዎችን ሲያነቃቃ በአንፃሩ የኢትዮ ኤሌትሪክን የመጫወት ፍላጎት አውርዶት በተሰራውም ስህተት የአሰልጣኝ ኢየሩሳሌም ነጋሽን ክፉኛ አስቆጥቷል። ይሄም ቢሆን በ76ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ጽዮን ፈየራ በግንባር በመግጨት ጎል አስቆጥራ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያደርጉትን ጥረት በተወሰነ መልኩ ከፍ አድርጎታል። በቀሩት 14 ደቂቃዎች አዳማዎች በጥንቃቄ እየተከላከሉ በመልሶ ማጥቃት የጎል አጋጣሚዎችን የፈጠሩ ሲሆን በተለይ አጥቂዋ ሴናፍ ዋቁማ በጨዋታው ሐት-ትሪክ መስራት የምትችልበትን አጋጣሚ ሳትጠቀምባቸው የቀረቻቸው ሁለት አጋጣሚዎች ለአዳማዎች የሚያስቆጩ ነበሩ። እንዲሁም ተቀይራ የገባችው የአዳማዋ ዮዲት መኮንን ያገኘችውን የግብ አጋጣሚዎች ሳትጠቀም ቀርታለች። በመጨረሻም ጨዋታው በባለ ሜዳዎቹ አዳማ ከተማዎች 2 – 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጥረት ኮርፖሬት 0-1 ጌዴኦ ዲላ

(በሚካኤል ለገሠ)

ባህር ዳር ላይ ጌዲዮ ዲላን ያስተናገደው ጥረት ኮርፖሬት 1-0 ተሸንፏል። አምና ከሜዳው ውጪ ውጤታማ ጉዞ ያደረገው ጌዴኦ ዲላ ዘንድሮም በዚሁ አቋሙ መዝለቁን ቀጥሏል። ጨዋታው በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ቀዝቀዝ ብሎ የታየ ሲሆን ቀስ በቀስ ግን እየተጋጋለ በመሄድ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አስተናግዷል። ባለሜዳዎቹ ጥረት ኮርፖሬቶች ከዚህ ቀደም ከሚታወቁበት ኳስን ተቆጣጥሮ የመጫወት አቀራረብ ወደ ቀጥተኛ አጨዋወት በመቀየር ለጨዋታው የቀረቡ ሲሆን ተጋባዦቹ ደግሞ በፈጣኖቻቸው የመስመር ተጨዋቾች በመታገስ በጨዋታው አደጋዎችን ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል።

የጨዋታው የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራ በ17ኛው ደቂቃ በጌዲዮ ዲላዋ አጥቂ ረድዔት አስረሳኸኝ አማካኝነት ተደርጎ በጥረቷ ግብ ጠባቂ ታሪኳ በርገና ተመልሷል። በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ይህቺው አጥቂ በደቂቃዎች ልዩነት የጥረቶች የግብ ክልል በመድረስ አስደንጋጭ ሙከራዎችን በተከታታይ ብትሰነዝርም ፍሬ ማፍራት ግን ሳትችል ቀርታለች። በእነዚህ ተደጋጋሚ ሙከራዎች የተደናገጡ የመሰሉት ጥረቶች ተረጋግተው መጫወት ተስኗቸው ስህተቶችን ሲሰሩ ታይተዋል። እነዚህን ስህተቶች በመጠቀም የተገኘውን ኳስም በመልሶ ማጥቃት በመውሰድ ጌዲዮዎች በረድኤት አስረሳኸኝ አማካኝነት ግብ በማስቆጠር በ21ኛው ደቂቃ መሪ ሆነዋል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላም መረጋጋት ያልቻሉት ጥረቶች በተለይ በመስመር በኩል የሚሰነዘርባቸውን ጫናን መቋቋም ተስኗቸው ታይተዋል። ግቧ ከተቆጠረች ከሁለት ደቂቃ በኋላ ወዲያው ወደ ጨዋታ ሊመለሱ የሚችሉበትን እድል በትመር ጠንክር አማካኝነት አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ከሜዳቸው ውጪ በመምጣት የበላይነት የወሰዱት ተጋባዦቹ ዲላዎችም በ27ኛው ደቂቃም መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉበትን እድል አግኝተው አምክነዋል። በዚህኛው ደቂቃ ድንቅነሽ በቀለ በረጅሙ የተላከላትን የአየር ላይ ኳስ በመጠቀም ከግብ ጠባቂዋ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ ኳሷን ቺፕ አድርጎ ለማስቆጠር ስትሞክር ታሪኳ በርገና ወደ ውጪ አውጥታባታለች።

በሁለተኛው አጋማሽ በአሰልጣኝ ሰርካዲስ የሚመሩት ጥረቶች በመጀመሪያው አጋማሽ የተወሰደባቸውን ብልጫ ሙሉ ለሙሉ በመቀልበስ የግብ ሙከራዎችንም አድርገዋል። በ54ኛው ደቂቃም ሀሳቤ ሙሶ ከቅጣት ምት ቡድኗን አቻ ለማድረግ ጥራ ሳይሳካላት ቀርቷል። በ63ኛው ደቂቃ ደግሞ መሠረት ገ/እግዚአብሄር ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርጋ ግብ ጠባቂ ምህረት ተሰማ አምክናዋለች።

ተደጋጋሚ ሙከራዎች ሲሰነዘርባቸው የአጥቂ መስመር ተጨዋቾቻቸውን በማስወጣት የተከላካይ እና የአማካይ ተጫዋቾችን ያስገቡት ጌዲዮዎች በእጃቸው የገባውን ሶስት ነጥብ አሳልፎ ላለመስጠት ጥረት አድርገዋል። በክፍት ጨዋታ ጎል ማስቆጠር የተሳናቸው ጥረቶችም ከቆሙ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ሙከራዎችን አድርገው ነበር። በዚሁ የጨዋታ እንቅስቃሴ ሀሳቤ ሙሶ ከርቀት የመታችውን ኳስ የጌዲዮ ዲላዋ ግብ ጠባቂ ምህረት ራሷን ለጉዳት አጋልጣ እንደምንም አድናዋለች። አሁንም ጫና ማድረጋቸውን የቀጠሉት ጥረቶች በ83ኛው ደቂቃ በጨዋታው የመጨረሻ ሙከራ በምስር ኢብራሂም አማካኝነት አድርገው መክኖባቸዋል። ጨዋታውም በጌዲኦ ዲላ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

*አዲስ አበባ ላይ የተደረጉትን ሁለት ጨዋታዎች ሪፖርት ከቆይታ በኋላ ይዘን እንቀርባለን


4ኛ ሳምንት
ቅዳሜ ታኅሳስ 6 ቀን 2011
መከላከያ 1-0 አርባምንጭ ከተማ
ጥረት ኮርፖሬት 0-1 ጌዴኦ ዲላ
አዳማ ከተማ 2-1 ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ኢትዮ ንግድ ባንክ 1-0 ድሬዳዋ ከተማ
እሁድ ታኅሳስ 7 ቀን 2011
ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ 09:00 ቅዱስ ጊዮርጊስ
ሀዋሳ ከተማ 09:00 አዲስ አበባ ከተማ