ሪፖርት | ባህር ዳር ከተማ በሜዳው ኢትዮጵያ ቡናን ረቷል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ሲደረጉ ባህር ዳር ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናገደው ባህር ዳር ከተማ በጃኮ አራፋት ብቸኛ ግብ አሸንፏል።

በዓመቱ ሁለተኛ የሜዳቸው ላይ ጨዋታቸውን ያደረጉት የጣና ሞገዶቹ በአምስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ሀዋሳን ከገጠመው ስብስባቸው የቀኝ መስመር ተከላካያቸውን ተስፋሁን ሸጋውን እና የፊት አጥቂያቸውን አህመድ ዋቴራን በሳላምላክ ተገኝ እና ጃኮ አራፋት በመቀየር ለጨዋታው ቀርበዋል። 563 ኪሜትሮችን አቆራርጠው የመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ደግሞ ወላይታ ዲቻን ከገጠሙበት የአምስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታቸው አማኑኤል ዮሃንስ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና ሚኪያስ መኮንንን በአልሃሰን ካሉሺያ፣ አህመድ ረሺድ እና ፍፁም ጥላሁን በመተካት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

 

 

በኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ የመሀል ዳኝነት በተመራው ጨዋታው በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች እንደ ደጋፊው ድባብ ሞቅ ብሎ የተደረገ ሲሆን ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችንም በጊዜ አስመልክቷል። በ3ኛው ደቂቃ ባህር ዳሮች ገና በጊዜ መሪ ሊሆኑ የሚችሉበትን አጋጣሚ በወሰኑ አሊ አማካይነት አግኝተው የነበረ ሲሆን ወሰኑ ከጃኮ አራፋት የተሻገረለትን የአየር ላይ ኳስ ነፃ ሆኖ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ዋቴንጋ ኢስማ አምክኖበታል። ለዚህች ሙከራ ምላሽ ለመስጠት በሚመስል መልኩ ቡናዎች ወዲያው በአልሃሰን ካሉሻ አማካኝነት ዕድል አግኝተው የነበረ ቢሆንም ኳሷ ኢላማዋን በመሳቷ መረብ ላይ ሳታርፍ ቀርታለች። በ8ኛው ደቂቃ ባህር ዳሮች ሌላ ዕድል በአምበላቸው ፍቅረሚካኤል አማካኝነት አግኝተው የነበረ ሲሆን ተጫዋቹ ከርቀት አክርሮ የመታትን የቅጣት ምት ዋቴራ ኢስማ አድኗታል። ከክፍት ጨዋታ ጎን ለጎን ከቆሙ ካሷችም የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቀጠሉት ባህረ ዳሮች በ20ኛው ደቂቃ ሌላ ጥሩ ዕድል አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። የቀድሞ ክለቡን የገጠመው አስናቀ ሞገስ ከቀኝ መስመር በኩል የተገኘውን የቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ጎል ቢሞክርም የኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች እንደምንም ተረባርበው አውጥተዋታል።


ከፈጣን የመስመር ለመስመር ሽግግሮች ወደ ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት አጨዋወታቸውን የቃኙት ባለሜዳዎቹ በመሀለኛው የሜዳ ክፍል ብልጫ በመውሰድ ተጋጣሚያቸው ላይ ጫና አሳድረው ተንቀሳቅሰዋል። ከተወሰደባቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ራሳቸውን ለማውጣት ጥረት ያደረጉት የዲዲዬ ጎሜስ ተጫዋቾች ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ጫናዎችን ለመቀነስ ሞክረዋል። ቢሆንም ግን የባህር ዳርን ፈጣን የማጥቃት አጨዋወት መቋቋም ተስኗቸው በ28 እና በ29ኛው ደቂቃ ሁለት አስደንዳጭ ሞከራዎች በዳንኤል ሃይሉ እና በግርማ ዲሳሳ ተሰንዝሮባቸዋል። ከረጃጅም ኳሶች በተጨማሪ ቡናዎች ከርቀት ሙከራዎችን እያደረጉ ጎል ለማስቆጠር የሞከሩ ሲሆን በ32ኛው ደቂቃም በአልሃሰን ካሉሻ አማካኝነት ሙከራ አድርገው መክኖባቸዋል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ወሰኑ ለጃኮ አራፋት ያሻገረለትን የአየር ኳስ ጃኮ አራፋት እራሱን ለጉዳት ዳርጎ በግንባሩ የገጨ ሲሆን ኳሷ ግብ ጠባቂውን አልፋ የግቡ ቋሚ መልሷታል። ይህቺን ሙከራ ሲያደርግ የተጎዳው ጃኮ አራፋት አገግሞ በመግባት በ43ኛው ደቂቃ ለግርማ ጥሩ ኳስ አመቻችቶ አቀብሎት ግርማ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ሁለቱም ቡድኖች ያለ ግብ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በእረፍት ሰዓት የስጦታ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት በስታዲየሙ የተደረገ ሲሆን የቀድሞ የባህር ዳር ከተማ እና የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች የነበረው ሁሴን ሰማን ከረጅም ጊዜያት የስደት ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ሃገሩ በመግባት ለ2010 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምርጥ ግብ ጠባቂ ሆኖ ለተመረጠው ምንተስኖት አሎ እና ለቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው ስጦታ አበርክቷል። ይህ የቀድሞ ተጨዋች ስጦታውን ለግለሰቦቹ ካበረከተ በኋላ ከኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች ማህበር እና ከባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ማህበር በተናጥል ስጦታዎችን ተቀብሏል። የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር ከሁሴን በተጨማሪ ለባህር ዳር ከተማ ህዝብ ስጦታ የሰጡ ሲሆን ስጦታውን የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን ተረክበውታል። ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር በተጨማሪ የባህር ዳር ከተማ ደጋፊዎች ማህበር ለኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር ፍቅር ይበልጣል የሚል ጥቅስ የታተመበት ምስል በስጦታነት አበርክተዋል።

ከእረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል ቡናዎች በመጠኑም ቢሆን ተሻሽለው ቀርበው ተረጋግተው ኳሶችን ተቆጣጥረው ለመጫወት ሞክረዋል። ሆኖም ቡናዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ባህር ዳር ከተማዎች ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝተው ግብ አስቆጥረዋል። በ56ኛው ደቂቃ ከመሀል መሬት ለመሬት የተላከውን ኳስ ግርማ ለመጠቀም ሲሮጥ ዋቴንጋ ኢስማ ከግቡ በመውጣት የተፋው ሲሆን የተተፋችውን ኳስ በትክክለኛው ሰዓት ትክክለኛው ቦታ ላይ የነበረው ጃኮ አራፋት ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ ወሰኑ ዓሊ ሌላ አጋጣሚ ከቅጣት ምት የፈጠረ ተጫዋች ሲሆን ለግቡ መቆጠር ምክንያት የሆነው ዋቴንጋ ኢስማ እንደምንም በማዳን ቡድኑን ክሷል። ከዚህኛው ሙከራ በኋላ ተጋባዦቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች ለውጦችን በማድረግ ተጭነው የተንቀሳቀሱ ሲሆን ፍሬ ለማፍራት ግን ተስኗቸው ታይቷል።


በመጀመሪያው አጋማሽ የተወሰደባቸውን የመሃል ሜዳ ብልጫ ለመረከብ ተጨማሪ የአማካይ ተጫዋች ቀይረው ያስገቡት ዲዲዬ ጎሜዝ ለውጣቸው ስኬታማ ሆኖ ኳስን ቢቆጣጠሩም ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ ግን ለማድረግ ተቸግረዋል። ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሚኪያስ መኮንን በ80ኛው ደቂቃ ከመስመር ተከላካዮች ጀርባ በመሮጥ ያገኛትን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ቢልካትም ኢላማዋን በመሳቷ መጨረሻዋ ውጪ ሆኗል። ያገኙትን ሦስት ነጥብ አሳልፎ ላለመስጠት ትግል ውስጥ የገቡት ባህር ዳሮች የአጥቂ መስመር ተጫዋቾቻቸውን በማስወጣት ወደ ኋላ አፈግፍገው ለመጫወት ሞክረዋል። ባህር ዳሮች ቢያፈገፍጉም ቡናዎች ከጨዋታው አንድ ነጥብ እንኳን ይዞ ለመውጣት የጣሩ ሲሆን ሙሉ ዘጠና ደቂቃው ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው በሚኪያስ አማካኝነት ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ጨዋታቸውን አጠናቀዋል።