በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ሀዋሳ ላይ ቀን 8:00 ሰዓት ደቡብ ፖሊስን ከባህር ዳር ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በጣና ሞገዶቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ባለሜዳዎቹ ደቡብ ፖሊሶች ወላይታ ድቻን ከገጠመው ስብስብ መካከል አራት ቅያሪዎችን በማድረግ በሳምሶን ሙሉጌታ፣ ዘርይሁን አንሼቦ፣ ቢኒያም አድማሱ እና መስፍን ኪዳኔ ምትክ አናጋው ባደግ፣ አዳሙ መሐመድ፣ ሙሉዓለም ረጋሳ እና ዘላለም ኢሳይያስን ሲጠቀሙ በባህር ዳር ከተማ በኩል ኢትዮጵያ ቡናን ከረታው ስብስብ ሙሉ በሙሉ ሳይቀይሩ የዛሬውን ጨዋታ ጀምረዋል። በጥቂት ደጋፊዎች እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ታጅቦ የተጀመረው ጨዋታ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ሳቢ ያልሆነ ነበር። ደቡብ ፖሊሶች በርካታ ያለቀላቸው አጋጣሚዎችን በማግኘት የተሻሉ ቢሆኑም ኳስን ከመረብ ለማገናኘት ግን በተደጋጋሚ ሲቸገሩ ተስተውሏል። በአንፃሩ ባህር ዳሮች በሙሉ ደቂቃው ያደረጉት ሶስት ሙከራ ብቻ ቢሆንም አንዷን ወደ ግብነት ቀይረው ውድ ሦስት ነጥቦችን አሳክተዋል።
በ5ኛው ደቂቃ ላይ የደቡብ ፖሊሱ በኃይሉ ወገኔ ያደረገው ሙከራ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ሲሆን ከዚህች አጋጣሚ በኋላ ፖሊሶች በርካታ እድሎችን አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። አጥቂው ኄኖክ አየለ ከግብ ጠባቂው ምንተስኖት ጋር በተደጋጋሚ ቢገናኝም በስተመጨረሻ ወደ ግብነት ለመቀየር ሲቸገር ሲስተዋል ከማዕዘን ምት በኃይሉ ወገኔ አሻምቶ ደስታ ጊቻሞ በግንባር በመግጨት የወጣበት እንዲሁም ብሩክ ኤልያስ በሁለት አጋጣሚዎች ሞክሮ ምንተስኖት አሎ የያዛቸው ኳሶችም ደቡብ ፖሊሶችን ዕድለኛ ያላስባሉ አስቆጪ ሙከራዎች ነበሩ። ባህር ዳሮች በአንፃሩ 38ኛው ደቂቃ ላይ ወሰኑ ዓሊ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ጃኮ አራፋት ሞክሮ በቀላሉ ዳዊት አሰፋ ከያዘበት ክስተት ውጭ ተጨማሪ ይህ ነው የሚባል ጠንካራ ሙከራን በዚህ አጋማሽ ማድረግ አልቻሉም።
ከእረፍት መልስ ባህር ዳር ከተማዎች በመጀመሪያ አጋማሽ ካሳዩት ደካማ እንቅስቃሴ አሻሽለው ሲገቡ እና ፖሊሶች ግን አሁንም የግብ በሩን በተደጋጋሚ በመፈተሹ ረገድ የተሻሉ የነበሩ ቢሆኑም በግብ ጠባቂው ምንተስኖት አሎ ጥረት ግብ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ባህርዳሮች ጥረታቸው በጎል ታጅቦ 64ኛው ደቂቃ ላይ ወሰኑ ዓሊ የግሉን ጥረት ተጠቅሞ በግራ የፖሊስ የግብ ክልል እየገፋ ገብቶ የዳዊት አሰፋን መውጣት ተመልክቶ በማስቆጠር እንግዶቹን ቀዳሚ አድርጓል።
ባህርዳሮች ከዚህች ግብ በኋላ ውጤታቸውን ለማስጠበቅ በመከላከሉ ላይ ሲጠመዱ ደቡብ ፖሊሶች በበረከት ይስሀቅ፣ ብሩክ ኤልያስ፣ አናጋው እና የተሻ አማካኝነት ተጨማሪ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለዋል። በ80ኛው ደቂቃ አናጋው ባደግ የሰጠውን ኳስ መስፍን ኪዳኔ አገባው ሲባል ምንተስኖት የመለሰበት እና በረከት ይስሀቅ አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጭ የተባለበት አጋጣሚዎችም አስቆጪ ነበሩ።
ጨዋታው በባህር ዳር ከተማ 1-0 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ከሜዳቸው ውጪ ሁለተኛ ድላቸውን ማስመዝገብ የቻሉት የጣና ሞገዶቹ በ11 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለዋል።