በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዲቪዚዮን አምስተኛ ሳምንት ዛሬ ሦስት ጨዋታዎች ተደርገው ጌዲኦ ዲላ ጥሩነሽ ዲባባን ሲረታ አርባምንጭ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ ድሬዳዋ ከተማ ከጥረት ኮርፖሬት ነጥብ ተጋርተዋል፡፡
አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አስተናግዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል። የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ በታየበት የመጀመርያው አጋማሽ የሚጠቀስ ሙከራ የተደረገው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ይህም በ20ኛው ደቂቃ የንግድ ባንኳ ተከላካይ ሰብለ ቶጋ የተከላካዮችን መዘናጋት ተከትሎ ከመሐል ይዛ በመውጣት ወደ ጎሉ መትታ ወደ ውጪ የወጣባት ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ ንግድ ባንኮች የመስመርና የፊት አጥቂዎችን በመቀየር ተጭኖ ለመጫወት ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም አማካኝነት በረሂማ ዘርጋው፣ ሰናይት ባሩዳ እና ሰብለ ቶጋ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ሲሞክሩ ቆይተው 53ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ብርቱካን ገ/ክርስቶስ ያሻገረችውን ኳስ ብዙዓየሁ ታደሰ ወደ ጎሉ አክርራ በመምታት ወደ ጎል ቀይራ ባንክን ቀዳሚ አድርጋለች።
62ኛው ደቂቃ ላይ ብርቱካን ገ/ክርስትስ ከረጅም ርቀት አክርራ መታ ወደ ውጪ የወጣው፣ 65ኛ ደቂቃ ላይ ረሂማ በግንባሯ ገጨረታ የወጣባት የሚጠቀሱ ሙከራዎች ሲሆኑ በባለሜዳው አርባምንጭ ደግሞ በሰርካለም ካሳ ከተደረጉ ሁለት ሙከራዎች በቀር ሌላ አስደጋጭ ሙከራ ለማየት ቀጣይ 10 ደቂቃዎች መጠበቅ ግድ ነበር። 72ኛው ደቂቃ ላይ የተሻማውን የማዕዘን ምት ሰርካለም በግንባሯ ገጭታ ወደ ጎል ሲያመራ ብርቱካን ገብረክርስቶስ በእጅ በመንካቷ በቀይ ካርድ ስትወጣ የፍፁም ቅጣት ምትም ለአርባምንጭ ከተማ ተሰጥቷል። ሰርካለም ባሳም ወደ ጎል በመቀየር የጨዋታውን ውጤት 1 ለ 1 እንደሆን አስችላለች።
ከዚህ ግብ መቆጠር በኋላ አርባምንጮች አጥቅተው ለመጫወት ቢሞክሩም የተጫዋች ቁጥር ብልጫን ተጠቅመው የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የሚችሉበትን አጋጣሚ ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በአንፃሩ አንድ ተጫዋች በቀይ የወጣባቸው ንግድ ባንኮች በረሂማ ዘርጋው የሚደረጉ ሙከራዎች ኢላማቸውን ቢጠብቁ ኖሮ ዉጤቱን ማስቀር ይችሉ ነበር። አርባምንጭ ከተማዎችም ውጤቱን ለማስጠበቅ ያደረጉት ትግል ተሳክቶላቸው ጨዋታው አንድ አቻ ተጠናቋል።
ዲላ ላይ ጌዲኦ ዲላ ከመመራት ተነስቶ ጥሩነሽን ዲባባ አካዳሚን 4-2 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ገና በሁለተኛው ደቂቃ ላይ ባለሜዳው ጌዲኦ ዲላ በመሰረት ወርቅነህ አማካኝነት ቀዳሚ ቢሆንም በሶስት ደቂቃ ልዩነት የዲላ ግብ ጠባቂ እና ተከላካይ ስህተትን የተመለከቱት ኚቦኝ የን እና ቅድስት በላቸው አከታትለው አስቆጥረው ጥሩነሽ ዲባባን መሪ ማድረግ ችለዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል 43ኛ እና 44ኛው ደቂቃ ላይ ፀባኦት መሐመድ በፍፁም ቅጣት ምት እንዲሁም መሠረት ወርቅነህ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኑ ሶስተኛዋን ግብ አስቆጥረው ወደ መሪነት ጌዲኦ ዲላ መመለስ ችለዋል። ከእረፍት መልስ ደግሞ 61ኛው ደቂቃ ላይ መንፈስ መችኔ ተጨማሪ ግብ አስቆጥራ ጨዋታው በጌዲኦ ዲላ 4-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡
ድሬዳዋ ከተማ ሐረር ላይ ጥረት ኮርፖሬትን ገጥሞ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል። አማካይዋ አዲስ ንጉሴ ለጥረት ኮርፖሬት ስታስቆጥር መቅደስ ማስረሻ የድሬዳዋ ከተማን ጎል ያስቆጠረች ተጫዋች ናት።
የመጀመርያ አምስት ደረጃ የያዙ ቡድኖች
ደረጃ. ክለብ ተጫ (ልዩ) ነጥብ
1. ንግድ ባንክ 5 (+6) 13
2. መከላከያ 5 (+5) 12
3. ጌዴኦ ዲላ 5 (+4) 12
4. አዳማ ከተማ 4 (+4) 10
5. ሀዋሳ ከተማ 5 (+5) 8