የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን አምስተኛ ሳምንት ከትላንት ቀጥሎ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ሲካሄዱ አቃቂ ቃሊቲ እና መቐለ 70 እንደርታ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል።
መቐለ ላይ ልደታ ከ/ከተማን ያስተናገደው መቐለ 70 እንደርታ 3-1 በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል። ብዙም ሳቢ እንቅስቃሴ ባልታየበት የመጀመርያ አጋማሽ የጨዋታው የመጀመርያው መከራ ለማድረግ 15 ደቂቃዎች ለመጠበቅ ግድ ብሎ ነበር። የልደታዋ ነፃነት ደርቤ ከሳጥኑ ጠርዝ የመታችው ኳስ የመቐለዋ ግብ ጠባቂ ምብራቅ አባዱ በቀላሉ አድናዋለች። በጨዋታው ከተጋጣምያቸው አንፃር ሲታይ የተሻለ ወደ ግብ ሲደርሱ የታዩት መቐለዎች በአስራ አራተኛው ደቂቃ ላይ ዮርዳኖስ በርሀ ከመስመር የተላከችላት ኳስ ተጠቅማ ባስቆጠረችው ጎል ቀዳሚ ሆነዋል።
ግብ ካስተናገዱ በኋላ ረጃጅም ኳሶች ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ የታዩት የልደታ ተጫዋቾች ብዙም ሳይቆዩ በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገችው እድላዊት ለማ በ16ኛው ደቂቃ ከረጅም ርቀት ባስቆጠረችው ጎል አቻ መሆን ችለዋል። በጨዋታው ከባለሜዳዎቹ መቐለዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ማሳካት ያልቻሉት ልደታዎች ንፁህ የጎል እድል ከመፍጠር ግን አልቦዘኑም ከነዚህ ውስጥ ቤተልሄም አሰፋ በሁለት አጋጣሚዎች የፈጠረቻቸው ዕድሎች ይጠቀሳሉ በተለይም ተጫዋችዋ ከርቀት መትታ ምብራቅ አባዲ ጨርፋ የወጣችው ልደታዎች አቻ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ነበረች። በመጀመርያ አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥር ሙሉ ብልጫ የወሰዱት ባለሜዳዎቹ መቐለዎች በ43ኛው ደቂቃ ላይ በአማካይዋ አበባ ገ\መድህን ግብ አስቆጥረው እየመሩ ወደ እረፍት አምርተዋል።
ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ትንሽ የግብ እድሎች የተፈጠሩበት ነበር። በልደታዎች በኩል እድላዊት ለማ በጥሩ ሁኔታ ይዛ ገብታ ፍረወይኒ አበራ ደርሳ ያስጣለቻት ሙከራ የተሻለ ለጎል የቀረበች ስትሆን በባለሜዳዎቹ መቐለዎች በኩልም ዮርዳኖስ በርሀ በሁለት አጋጣሚዎች የፈጠረቻቸው እድሎች ይጠቀሳሉ። በዚ መሃል በጨዋታው የመቐለን የአጥቂ ክፍል በጥሩ ሁኔታ ስትመራ የነበረችው ዮርዳኖስ ምዑዝ ከርቀት ግሩም ግብ አስቆጥራ የመቐለን የግብ መጠን ወደ ሦስት ከፍ ማድረግ ችላለች። በጨዋታው የመቐለዋ ሰላም ተኽላይ እና የልደታ ክ/ከተማዋ ዕድላዊት ለማ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉ ተጫዋቾች ናቸው።
አዲስ አበባ ስታድየም ላይ መሪው አቃቂ ቃሊቲ ር/ከተማ ከቂርቆስ ክ/ከተማ ያደረገውን ጨዋታ 2-0 አሸንፏል። 09:00 በተደረገው በዚህ ጨዋታ ሁለቱንም የአቃቂ ቃሊቲ የማሸነፍያ ጎሎች ያስቆጠረችው ሠላማዊት ጎሳዬ ናት። ከአምስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ነጥብ የጣለው አቃቂ ቃሊቲ ድሉን ተከትሎ በ13 ነጥብ ሊጉን መምራቱን ቀጥሏል።
ትላንት በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ፋሲል ከነማ በቤተልሔም አምሳሉ (2) እና እሸት የሻምበል ጎሎች 3-2 ሲያሸንፍ ሻሸመኔ ከተማ ከሜዳው ውጪ ቦሌ ክ/ከተማን በብርቄ አማሬ ብቸኛ ጎል 1-0 አሸንፏል፡፡