ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ሀዋሳ ከተማን በመርታት ደረጃውን አሻሽሏል

ሲዳማ ቡና እና ሀዋሳ ከተማን ያገናኘው የሊጉ የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታ በአዲስ ግደይ የፍፁም ቅጣት ምት በሲዳማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

የሮድዋ ደርቢ የወትሮው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት የሚታይበት እንዳይሆን የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ማለዳ ላይ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ጨዋታውም በርካታ ቁጥር ያለው ተመልካች የታደመበት ነበር። በቅርቡ ህይወታቸውን ላጡት የሲዳማ ደጋፊዎች የህሊና ፀሎት በማድረግ ከስጦታ ልውውጦች በኋላ በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ታጅቦ የጀመረው ጨዋታ 10 ያህል ደቂቃዎችን ዘግይቶ ነበር።

በስድስተኛው ሳምንት ሽረ ላይ አቻ የተለያዩት ሲዳማ ቡናዎች ከተጠቀሙበት አሰላለፍ ውስጥ መሀመድ ናስርን በፀጋዬ ባልቻ ፣ ወንድሜነህ ዓይናለምን በዳግም ንጉሴ ተክተው ሲገቡ ሀዋሳ ከተማዎች በተመሳሳይ ስሁል ሽረን በሰፊ የግብ ልዩነት ከረቱበት ጨዋታ ሶሆሆ ሜንሳን በተክለማርያም ሻንቆ ፣ ታፈሰ ሰለሞንን በነጋሽ ታደሰ እንዲሁም አዳነ ግርማን በደስታ ዮሀንስ በመለወጥ ጨዋታውን ጀምረዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በብቃት የመሩት እና ስድስት የማስጠነቀቂያ ካርዶች የመዘዘበት ይህ ጨዋታ ሳቢ ያልሆነ የመጠናናት ዓይነት እንቅስቃሴ እና ቶሎ ቶሎ የሚቆራረጡ ኳሶች የበዙበት ነበር። ሁለቱም ቡድኖች በረጃጅም እና ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ለመጫወት ያደረጉት ጥረትን ብንመለከትም እምብዛም ፍሪያማ አልነበሩም። የመጀመሪያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች የተሻለ የጨዋታ ሂደትን ያሳዩበት ነበር። 6ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ ዳዊት ተፈራ መሀል ለመሀል ሰጥቶት አዲስ ግደይ ወደ ግብ ሲመታት ተክለማርያም ሻንቆ የያዘበት የመጀመሪያው የግብ ሙከራ ነበረች። ሲዳማ ቡናዎች በረጃጅሙ ከአማካይ መስመር ተሰላፊዎቻቸው አዲስ ግደይ እና ሀብታሙ ገዛኸኝን ያነጣጠሩ ኳሶችን እያሻገሩ ለመጫወት ሲሞክሩ ሀዋሳ ከተማዎች የዳንኤል ደርቤ ጥረት የሆኑ ግን ደግሞ የባከኑ ተሻጋሪ ኳሶችን ሲጠቀሙ ታይተዋል።


በፊት አጥቂነት ተሰልፎ የነበረው አዲስ ግደይ ወደ ቦታው ከተመለሰ በኋላ የተሻለ እንቅስቃሴን ማድረግ ቢችልም እርሱ እና ፀጋዬ ባልቻ እንደሌላው ጊዜ ያገኙትን አጋጣሚ እንዳይጠቀሙ የሀዋሳው ጋናዊ ተከላካይ ላውረንስ ላርቴ ልዩ ብቃት አስደናቂ ነበር። ከላውረንስ በተጨማሪ የግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆም ያሳየው አቋም መልካም ነበር። መሀል ሜዳ ላይ ሀዋሳዎች የታፈሰ ሰለሞን ያለመኖር የጎዳቸው ይመስላል። በአንፃሩ የግርማ በቀለ የኃይል አጨዋወት ሲዳማዎች ይህን የተጋጣሚያቸውን ደካማ ጎን እንዳይጠቀሙ አድርጓል። በ26ኛው ደቂቃ ፍቅረየሱስ ለዳንኤል ሰጥቶት ከግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ በቀላሉ ያመከናት እና 40ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ከመስመር አሻግሮ ደስታ እና እስራኤል ሲገባበዙ ያመከኗት ኳስ በሀዋሳ በኩል ተጠቃሽ መከራዎች ነበሩ። ሲዳማዎችም በልማደኛው አዲስ ግደይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ማድረግ ችለዋል። ተጫዋቹ ግብ አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጭ ተብሎበትም ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ አልፎ አልፎ ወጣ ገባ የሚል እንቅስቃሴ የታየ ሲሆን ሲዳማዎች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ብልጫን መውሰድ ባይችሉም ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት በማድረጉ የተሳካ የሆነላቸው ኃይቆቹ ደግሞ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ብልጫ መውሰድ ችለዋል። 47ኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ዮሃንስ ከርቀት አክርሮ መትቶ ተክለማርያም ሻንቆ ባወጣበት ኳስ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ቀዳሚ ሙከራ ያደረጉት ሲዳማዎች ነበሩ። በመልሶ ማጥቃት በፍጥነት ወደ ሲዳማ የግብ ክልል የደረሱት ሀዋሳዎች በደስታ ዮሀንስ አማካኝነት መልካም አጋጣሚን ቢያገኙም በቀላሉ አምክኗታል። ደስታ በመስመር በኩል የሚጥላቸው ኳሶች እጅግ አስደንጋጭ ቢባሉም ወደ ግብነት ለመለወጥ ግን አልታደሉም።


74ኛው ደቂቃ ዳዊት ተፈራ ከመሀል ሜዳ ካሻገራት ኳስ አዲስ ግደይ እና ተክለማርያም ሻንቆ በተገናኙበት ቅፅበት ግብ ጠባቂው ጥፋት በመስራቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አዲስ በመምታት አስቆጥሯል። ግቧ ለፈጣኑ የመስመር አጥቂ የዓመቱ ስድስተኛ ግቡ ሆናለታለች። ከግቧ በኃላ ዳግም ሲዳማዎች በአዲሱ ተስፋዬ አማካኝነት በቀላሉ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድል አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ሀዋሳዎችም አቻ ለመሆን የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ሁለት ጊዜ በገብረመስቀል ዱባለ
መጠቀም ሳይችሉ ጨዋታው በሲዳማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።