በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት የመጀመርያ ጨዋታ ሀዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ጋብዞ 1-0 ተሸንፏል።
ደቡብ ፖሊስ ወደ አዳማ አምርቶ 1-0 ከተሸነፈው ስብስቡ የሶስት ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ ዘሪሁን አንሼቦ፣ አዲስዓለም ደበበ እና መስፍን ኪዳኔን በማሳረፍ ሙሉዓለም ረጋሳ፣ ኤርሚያስ በላይ እና በረከት ይስሀቅን ሲጠቀም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ቡና ያለ ጎል አቻ ከተለያየበት ጨዋታ አራት ለውጦችን አድርጎ በፓትሪክ ማታሲ (ቀይ)፣ ሳላሀዲን በርጊቾ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና አብዱልከሪም መሐመድ ምትክ ለዓለም ብርሀኑ፣ ፍሬዘር ካሳ፣ ታደለ መንገሻ እና በኃይሉ አሰፋን በቀዳሚው አሰላለፍ በማካተት በፌዴራል ዳኛ ዮናስ ካሳሁን መሪነት ጨዋታው ተከናውኗል።
በጨዋታው ቢጫ ለባሾቹ ደቡብ ፖሊሶች ብልጫ ወስደው የተጫወቱ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተዳክሞ የታየበት ነበር። በ2ኛው ደቂቃ በግራ በኩል አቤል ያለው በቀጥታ ወደ ጎል መትቶ ዳዊት አሰፋ ያዳነበት አጋጣሚ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ስትሆን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ በረከት ይስሀቅ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል የላካት ኳስ ፍሬዘር ካሳ ጨርፏት ለጥቂት ግብ ከመሆን ተርፋለች። 6ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ከሙሉዓለም መስፍን እግር ስር የተነሳችውን ኳስ አቡበከር ሳኒ በግራ መስመር ገብቶ ወደ ግብ ሲልካት አማካዩ ሙሉዓለም ረጋሳ ለማውጣት ሲሞክር በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸናፊ ያደረገች ግብ ገና በጊዜ ተቆጥራለች።
ከግቧ መቆጠር በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊሶች አስቻለው ታመነ እና ታደለ መንገሻ በግላቸው ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውጪ በደቡብ ፖሊስ ብልጫ ተወስዶባቸዋል። ሙሉዓለም ረጋሳ 28ኛው ደቂቃ ላይ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ዘላለም ኢሳይያስ ክፍት አጋጣሚን አግኝቶ ያመከናት ኳስ የምትጠቀስ አስቆጪ ሙከራ ስትሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው ከተከላካይ በረጅሙ በሚለጉ ኳሶች ለሳላሀዲን ሰዒድ ለማድረስ ጥረት ሲያደርጉ የነበረ ቢሆንም የደቡብ ፖሊሱ ተከላካይ ደስታ ጊቻሞ ሲያስጥለው ታይቷል። የመጀመርያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ደቂቃ ሲቀረው በኃይሉ አሰፋ ጥሩ ኳስ ቢያገኝም የቀድሞው ክለቡን የገጠመው አበባው ቡጣቆ እንደምንም ተንሸራቶ አውጥቶበታል፡፡ ወደ መልበሻ ክፍል ከማምራታቸው በፊት በስታዲየሙ በደጋፊዎች መካከል ፀብ የተነሳ የነበረ ቢሆንም ሳይባባስ በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አሁንም የደቡብ ፖሊስ የእንቅስቃሴ የበላይነት የታየበት ቢሆንም ፈረሰኞቹ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመመለስ ጥረት ያደረጉበት ነበር። በኃይሉ አሰፋ ከማዕዘን ምት የላካትን ኳስ አስቻለው በግንባር በመግጨት ሞክሮ ወደ ውጪ ሲወጣበት በ58ኛው ደቂቃ ሳላሀዲን ሰዒድ ከታደለ መንገሻ ያገኛትን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ መቶ ግብ ጠባቂው ዳዊት አሰፋ አድኖበታል። እነዚም ሁለት ሙከራዎችም ጊዮርጊሶች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረጉትን ጥረት ያሳዩ ነበሩ።
ግብ ለማስቆጠር በተለይ የመጨረሻዎቹን 30 ደቂቃዎች አጥቅተው መጫወት የቻሉት ደቡብ ፖሊሶች በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም ወደ ግብነት ለመለወጥ ግን እጅጉን ተዳክመው የታዩበት ነበር። 76ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት አበባው ቡጣቆ መትቶ ግብ ጠባቂው ለዓለም ብርሀኑ ያወጣው፣ ዘላለም ኢሳይያስ ያለቀለት ኳስ አግኝቶ በቀላሉ ያመከነው እድሎችም የሚጠቀሱ ነበሩ። 80ኛው ደቂቃ ላይ አናጋው ባደግ ወደ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ያሻገራት ኳስ በተከላካዩ ፍሬዘር ካሳ በእጅ በመነካቷ የፍፁም ቅጣት ምት ይገባናል በማለት የእለቱን ዋና ዳኛ ተመልካቹም ሆነ ተጫዋቾቹ ከፍተኛ ተቃውሞን ያሰሙበት ሲሆን በዚህም ሂደት አራት ደቂቃዎች ለመቋረጥ ተገዶ ነበር። በጭማሪ ደቂቃዎች ደቡብ ፖሊሶች በበኃይሉ እና ዘላለም ሙከራ ሲያደርጉ በጊዮርጊስ በኩል ተቀይሮ የገባው ጌታነህ ከበደ ለግብ የቀረበ ሙከራ ቢያደርግም ጨዋታው ተጨማሪ ጎል ሳያስተናግድ በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጪ የመጀመርያ ድሉን ሲያሳካ ደቡብ ፖሊስ በተከታታይ አምስተኛ ሽንፈቱን አስተናግዷል ፡፡