ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

ከ9ኛው ሳምንት መርሐ ግብር መካከል ድሬዳዋ ባህር ዳርን በሚያስተናግድበት ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን መረጃዎች አጠናቅረናል።

ከአሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ጋር ከተለያዩ በኋላ ከሶዶ አንድ ነጥብ ይዘው የተመለሱት ድሬዳዋ ከተማዋች ነገ 09፡00 ላይ በተመሳሳይ ከአቻ ውጤት የመጣው ባህር ዳር ከተማን ያስተናግዳሉ። በበርካታ ውዝግቦች ከተዘጋው የሶዶው ጨዋታ አስቀድሞም ከደቡብ ፖሊስ በተመሳሳይ 1-1 ተለያይተው የነበሩት ድሬዎች በጨዋታ በአማካይ አንድ ነጥብ በመሰብሰብ በስድስት ነጥቦች አስራ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ከተጋጣሚያቸው ጋር እኩል ስድስት ጨዋታ አድርገው በሰባት ደረጃዎች ተሽለው የሚገኙት ባህር ዳሮች ሳምንት መከላከያን አስተናግደው ማሸነፍ ባይችሉም ያለነሸነፍ ጉዟቸው እንዲደናቀፍ ግን አልፈቀዱም። ባህር ዳሮች ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማሳካት ከቻሉ የሌሎች ክለቦችን ውጤት ጠብቀው ወደ አንደኝነት ከፍ የሚሉበት ዕድልም ሊኖር ይችላል። 

ባለሜዳዎቹ ድሬዳዋ ከተማዎች ከራምኬል ሎክ በቀር ቀሪው ስብስባቸው ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ሆኖ ለነገው ጨዋታ ሲደርስ በባህር ዳሮች በኩል ግን በርካታ ተጫዋቾች ከጨዋታው ውጪ ሆነዋል። በዚህም ቡድኑ ደቡብ ፖሊስን ሲገጥም የተጎዱት ወሰኑ ዓሊ እና ጃኮ አራፋት ከጉዳታቸው ያላገገሙ ሲሆን አምበሉ ፍቅረሚካኤል አለሙ እና የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሳለአምላክ ተገኝም ለነገው ጨዋታ አይደርሱም።

ድሬዳዋ ከተማ ዘንድሮ በአሰልጣኝ ስምኦን ዓባይ እየተመራ በሜዳው በሚያደርገው የመጀመሪያ ጨዋታ የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የሚታይበት አቀራረብ እንደሚኖረው ይጠበቃል። ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመግባት የመጀመሪያ ምርጫዎቻቸው በሆኑት የቡድኑ የመስመር አማካዮች በኩል ጫና ለመፍጠር እንደሚሞክሩ የሚጠበቁት ድሬዎች የተጋጣሚያቸው የመስመር ተከላካዮች አናሳ የማጥቃት ተሳትፎ ነገሮችን ቀላል ላያደርግላቸው ይችላል። በመጨረሻው የሜዳው ጨዋታ ላይ ንፁህ የግብ ዕድሎችን ወደ ውጤት የመቀየር ችግር የተስተዋለባቸው አጥቂዎቹም ከባህር ዳር ጠንካራ የኋላ መስመር ጋር ከባድ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል።

በአንፃሩ ኳስን መስርቶ መጫወት ምርጫቸው የሆነው ባህር ዳሮች የባለሜዳዎቹን የመስመር ጥቃት በጥንቃቄ በማቆም በሁለቱ የማጥቃት አማካዮቻቸው እንቅስቃሴ ላይ ተመስርተው ወደ ድሬ የሜዳ አጋማሽ ለመግባት እንደሚጥሩ ይታሰባል። ይሁን እንጂ ቡድኑ ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ከገባ በኋላ ወደ ግራ አመዝናኖ የሚያጠቃ መሆኑ የግራማ ዲሳሳን እና ገናናው ረጋሳ ፍልሚያ ተጠባቂ ያደርገዋል። ከምንም በላይ ግን ባህርዳር  በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በተከታታይ ያስገባቸው ከነበሩ ተጫዋቾቹ ውስጥ አራት የሚሆኑትን በጉዳት ማጣቱ የቡድኑን ውህደት እንዳይቀንሰው የሚያሰጋው ነው።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ጨዋታው ሁለቱ ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ የሚገናኙበት የመጀመሪያ ጨዋታ ይሆናል።

–  ድሬዳዋ ከተማ እስካሁን ከሰበሰባቸው ስድስት ነጥቦች ውስጥ አራቱን በሜዳው ካደረጋቸው ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ችሏል።

– ከሜዳ ውጪ ጥሩ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ባህር ዳሮች ከሦስት ጨዋታዎች ውስጥ ሁለቱን አሸንፈው በአንዱ ነጥብ ተጋርተዋል። በአጠቃላይ እስካሁን በስድስት ጨዋታዎች መረባቸውን ያስደፈሩትም ሁለት ጊዜ ብቻ ነበር። 

ዳኛ

– ሰባተኛው ሳምንት ላይ መቐለ 70 እንደርታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተገናኙበትን ጨዋታ በብቸኝነት የመራው ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በዚህ ጨዋታ ላይ በመሀል ዳኝነት ተመድቧል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ገናናው ረጋሳ – አንተነህ ተስፋዬ – ፍቃዱ ደነቀ – ሳሙኤል ዮሃንስ

ሚኪያስ ግርማ – ፍሬድ ሙሺንዲ –  ምንያህል ይመር – ረመዳን ናስር

ኢታሙና ኬይሙኒ – ኃይሌ እሸቱ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ምንተስኖት አሎ

ተስፋሀን ሸጋው – ወንድሜነህ ደረጄ  – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ

ዳንኤል ኃይሉ  –  ታዲዮስ ወልዴ – ኤልያስ አህመድ

ዜናው ፈረደ – ፍቃዱ ወርቁ –ግርማ ዲሳሳ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *