ሴቶች 1ኛ ዲቪዝዮን | አዳማ ነጥብ ሲጥል መከላከያ እና አአ ከተማ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ሰባተኛ ሳምንት ዛሬ በአዲስ አበባ ስቴዲዮም እና ክልል ከተሞች ቀጥሎ ሲካሄድ መከላከያ እና አዲስ አበባ ከተማ አሸንፈዋል። አዳማ ከተማ ደግሞ ወደ መሪነት የመመለስ እድሉን አምክኗል።

የአዲስ አበባ ስታድየም ውሎ

(በዳንኤል መስፍን)

በአዲስ አበባ ስታዲየም 08:00 ላይ የጀመረው የአአ ከተማ እና ቅዱሰ ጊዮርጊስ ጨዋታ በአአ ከተማ 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ገና በጨዋታው ጅማሬ 2ኛ ደቂቃ ላይ የአአ ከተማዋ ሔለን መሰለ አማካኝነት ከግብ ጠባቂዋ ጋር ብቻ ለብቻ ተገናኝታ ባመከነችው ኳስ ነበር የጎል ሙከራ መመልከት የጀመርነው። በአንድ ሁለት ቅብብል ረጃጅም ኳሶችን ወደ ጎል በመጣል በፍጥነት የሚደርሱት አዲስ አበባዎች በ13ኛው ደቂቃ ሜላት ደመቀ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን በግንባሯ በመግጨት ጎል አስቆጥራ አዲስ አበባዎችን ቀዳሚ ማድረግ የቻለችው።  ከጎሉ መቆጠር በኋላ ብዙም ማራኪ ሳይሆን በቀጠለው በዚህ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የሜዳውን ክፍል አጥብብው ለመጫወት የሚያደርጉት ጥረት በተክለ ሰውነት እና በግዝፈት ላቅ የሚሉት የአዲስ አበባ ተጫዋቾች ኳሱን በመንጠቅ ወደ ፊት እንዳይሄዱ በማድረግ መቆጣጠራቸው በፈረሰኞቹ በኩል ለጎል የቀረበ ሙከራ እንዳያደርጉ ሆኗል። አዲስ አበባዎች በብቸኛዋ የፊት አጥቂያቸው ሔለን መሰለ አማካኝነት ጎል ባያስቆጥሩም አደጋ ይፈጥሩ ቢፈጥሩም የተለየ ነገር ሳንመለከት እረፍት ወጥተዋል።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻሉ የኳስ ቅብሎች እና የጎል ሙከራ  አሳይቶን በቀጠለው ጨዋታ በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ጎል ያመሩት አዲስ አበባዎች በ46ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂዋ ሔለን መሰለ ሁለተኛውን ጎል ስታስቆጥር ብዙም ሳይቆይ በ50ኛው ደቂቃ የመስመር ተከላካያዋ ፍሬወይኒ ገ/ፃድቅ ሦስተኛ ጎል አስቆጥራ የአዲስ አበባን የጎል መጠን ከፍ አድርጋዋለች። በተከታታይ በተቆጠረባቸው ጎሎች ተስፋ ሳይቆርጡ ጥሩ ኳስ መጫወት የቻሉት ፈረሰኞቹ 59ኛው ደቂቃ በአንበሏ ሶፋኒት ተፈራ አማካኝነት ከሳጥን ውጭ የተገኘውን ቅጣት ምት ለጥቂት ቢወጣባትም 62ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ ቀጥታ ምት የተመታችውን በተከላካዮች ተደርቦ የተገኘውን ኳስ ብርሃን ኃይለ ሦላሴ ጎል ስታስቆጥር የመስመር ዳኛው ከጨዋታ ውጭ ነው ቢልም የመሀል ዳኛዋ ጎል ብላ በማፅደቋ በተፈጠረው ውዝግብ አዲስ አበባዎች ተቃውሞ ቢያቀርቡም ጨዋታው ጎል ሆኖ ቀጥሏል። 

በጎሉ መቆጠር የተነቃቁት ጊዮርጊስ ተጨማሪ ጎል ፍለጋ ተጭነው ሲጫወቱ 72ኛው ደቂቃ የአዲስ አበባዋ ግብጠባቂዋ ሳሳሁልሽ ሥዩም ከግብ ክልል ውጭ ኳስ በእጅ በመንካቷ የዕለቱ ዳኛ በቀይ ካርድ ከሜዳ ውጭ ታስወጣታለች ሲባል በቢጫ ማስጠንቀቂያ ካርድ ማለፉ በተጫዋቾች በኩል ተቃውሞ አስነስቶባት ቅጣት ምቱንም ሳይጠቀሙበት ቀርቷል።  ሦስት ጎል አስቆጥረው በመምራታቸው የተቀዛቀዙት አዲስ አበባዎች ተቀይረው በገቡት አጥቂዎች አልፎ አልፎ በፎዚያ መሐመድ እና ቤዛዊት ተስፋዬ አማካኝነት ያልተሳኩ የጎል እድሎቸ ሲፈጥሩ ቆይተው በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ፎዚያ መሐመድ አራተኛ የማሳረጊያ ጎል አስቆጥራ ጨዋታው በአዲስ አበባዎች 4-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

10:00 የቀጠለው ሁለተኛ ጨዋታ መከላከያን ከኢትዮ ኤሌትሪክ ሲያገናኝ ጥሩ ፉክክር ተስተናግዶበት መከላከያ 2-0 አሸንፏል።  የጎል ሙከራ በማድረግ መከላከያዎች ቀዳሚ ነበሩ። በ3ኛው ደቂቃ ኤልሻዳይ ግርማ ከማዕዘን ምት የተሻገረን ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ ሆና ብታገኘውም ግብጠባቂዋ ገነት አንተነህ አድናባታለች። ብልጫ የወሰዱት መከላከያዎች 10ኛው ደቂቃ የኢትዮ ኤሌትሪክ ግብ ጠባቂ ገነት አንተነህ ከስድስት ሰከንድ በላይ በግብ ክልሏ ውስጥ ኳስ በእጇ በመያዝ በማዘግየቷ የተሰጠውን ሁለተኛ ቅጣት ምት እመቤት አዲሱ ብስለቷን ያሳየችበትን ግሩም ጎል አስቆጥራ መከላከያዎችን ቀዳሚ አድርጋለች።


19ኛው ደቂቃ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ግብ ጠባቂ በድንገት ሳይጠበቅ ወድቃ በፍጥነት የህክምና እርዳታ ተደርጎላት ጨዋታውም ከተወሰኑ ደቂቃዎች መቋረጥ የጨዋታው አንዱ ክስተት ሆኖ ጨዋታው ሲቀጥል ከሳጥን ውጭ የሚገኙ ቅጣት ምቶች በጠንካራ ምቷ አደጋ የምትፈጥረው የኢትዮ ኤሌትሪኳ የመስመር አጥቂ መሳይ ተመስገን በሁለት አጋጣሚዎች 21፣ 42ኛው ደቂቃ ላይ የተገኙትን ቅጣት ምቶች የመከላከያዋ ግብጠባቂ  ማርታ በቀለ እንደ ምንም ያወጣችባት ኳሶች ወደ ጎልነት ቢቀየሩ ኖሮ ኤሌትሪኮችን ወደ ጨዋታው መመለስ የሚችሉ የሚያስቆጩ አጋጣሚዎች ነበሩ። 

ከእረፍት መልስ በ47ኛው ደቂቃ አረጋሽ ካልሳ ከቅጣት ምት ያሻገረችውን ተከላካይዋ መሰሉ አበራ በግንባሯ በመግጨት የመከላከያን የግብ መጠን ወደ ሁለት አሳድጋለች። የኢትዮ ኤሌትሪክ ተከላካዮች በተደጋጋሚ የሚሰሩትን ስህተት ተከትሎ የመጀመርያ ተሰላፊ በመሆን ዛሬ የገቡት የመከላከያዎቹ አጥቂዎች አረጋሽ ካልሳ፣  ሄለን እሸቱ ፣ ሲሳይ ገ/ዋህድ ጎል መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎች ከትኩረት ማጣት እና ካለመረጋጋት የተነሳ ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። በዋናነት 59ኛው እና 64 ኛው ደቂቃ ላይ ሄለን እሸቱ  ያልተጠቀመችባቸው ኳሶች የመከላከያን የግብ መጠን ከፍ ማድረግ የሚችሉ ነበር። በሁሉም ረገድ ተዳክመው የቀረቡት ኢትዮ ኤሌክትሪክ በጨዋታው መጠናቀቂያ 89ኛው ደቂቃ ተቀይራ የገባችው ዓይናለም ወንድሙ ባዶ ጎል ተቻኩላ ከሳተችው ውጭ ምንም የጎል እድል መፍጠር ሳይችሉ መቅረታቸው ብቻ ሳይሆን ቡድኑ ብዙ ክፍተቶቹን በቀሪ ጨዋታዎች ማስተካከል እንደሚገባው የዛሬው ጨዋታ ማሳያ ነው። 90ኛው ደቂቃ ምስራች ላቀው ሌላ ሙከራ ብታደርግም ተጨማሪ ጎሎች ሳንመለከት ጨዋታው በመከላከያ የበላይነት 2-0 አሸናፊነት ተፈፅሟል።

የክልል ጨዋታዎች 

(በቴዎድሮስ ታከለ)

ድሬዳዋ ላይ በ10:00 ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን አዳማ ከተማን አስተናግዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቋል። አይዳ ዑስማን ለድሬዳዋ ከተማ፤ ሴናፍ ዋቁማ ለአዳማ ከተማ ጎሎቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው። 88ኛው ደቂቃ ላይ የድሬደዋ ከተማዋ ምስጋና አሰፋ በሳጥን ውስጥ ሴናፍ ዋቁማ ላይ ጥፋት በመስራቷ ፍፁም ቅጣት ምት ሲሰጥ ምስጋናም ለቀጥታ ቀይ ካርድ ተዳርጋለች። ሆኖም የፍፁም ቅጣት ምቱን ሴናፍ ዋቁማ ብትመታም አምክናለች፡፡

ዲላ ላይ ከከፍተኛ ሊግ ጨዋታ ቀጥሎ 10:00 ጌዲኦ ዲላን ከሀዋሳ ከተማ አገናኝቶ  2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተደምድሟል። ከአራት ጨዋታ ቅጣት የተመለሰችሁ አጥቂዋ ምርቃት ፈለቀ 16ኛው ደቂቃ እንዲሁም በ36ኛ ደቂቃ ደግሞ ነፃነት መና ሀዋሳን መሪ አድርገው የነበረ ቢሆንም በ44ኛው ደቂቃ ቤተልሄም በቀለ ጌዲኦ ዲላን ወደ ጨዋታ የመለሰች ግብ አስቆጥራ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት ለእረፍት ወተዋል። ከእረፍት መልስ 66ኛው ደቂቃ መሠረት ጌዲኦ ዲላን ነጥብ የተጋራበትን ግብ አስቆጥራ ጨዋታው 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የሀዋሳ ከተማዋ ተከላካይ ቅድስት ዘለቀ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዳለች።

አርባምንጭ ከተማ በሜዳው ጥሩነሽ ዲባባ ከተማን አስተናግዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት አጠናቋል። ማራኪ በነበረውና በርካታ ሙከራዎች በተስተናገዱበት ጨዋታ በመጀመርያዎቹ 10 ደቂቃዎች አርባምንጭ ከተማዎች በተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ማድረግ የቻሉበት ነበር። በአርባምንጭ በኩል በ2 እና 8ኛው ደቂቃ ላይ ቱሪስት ለማ እና ሰርካለም ባጫ ጥሩ የግብ እድል ቢያገኙም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በ16ኛው ደቂቃ የጥሩነሽ አካዳሚዋ ትንሳኤ ሻንጎ ወደ ጎል አክርራ የመታችው  ኳስ አቅጣጫውን ስቶ ቤተልሄም ሽመልስ ጋር ደርሶ  ቤተልሄም በአግባቡ ያገችውን እድል በመጠቀም የመጀመርያውን ጎል አስቆጥራ ጥሩነሽን መሪ ማድረግ ችላለች። ከዚህች ግብ መቆጠር በኃላ ግብ ለማስቆጠር ተጭነው ለመጫወት የሞከሩት አርባምንጭ ከተማዎች በመሰረት ማቲዮስ ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶችና በትሁን አየለ ሁለት ቅጣት ምቶች ሙከራዎችን ሲያደርጉ ቆይተው በ28ኛው ደቂቃ ላይ በሰርካካም ባሳ ግሩም ግብ  የአቻነቷን ጎል አስቆጥረው ጨዋታው 1-1 ሊሆን ችሏል፡፡ ሁለተኛ ጎል ለማስቆጠር ሁለቱም ክለቦች ተጭነው ቢጫወቱም የመጀመርያ አጋማሹን 1ለ1 በሆነ ውጤት አጠናቀዋል።

ሁለተኛው  አጋማሽ  ከመጀመርያው አጋማሽ እጅግ ቀዝቅዞና ድካም የታየበት በመሆኑ ይህ ነው የሚባሉ የግብ ሙከራዎችን ያስተናገደ አልነበረም። አርባምንጮች በስርካለም ባጫ ካደረጉት የ76ኛ ደቂቃ  ሙከራ ውጪ ምንም አይነት አስደንጋጭ ሙከራ ሳይደረግ ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *