በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ለ 6ኛ ሳምንት ከስድስቱ ጨዋታዎች አምስቱ ሲከናወኑ የመድን እና የሀላባ ጨዋታ ተቋርጧል። አራት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲደመደሙ ወልቂጤ በጎል ተንበሻብሿል።
የሀላባ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታ ምንም ግብ ሳያስተናግድ 76ኛው ደቂቃ ላይ ተቋርጧል። በርካታ የግብ ዕድል በተፈጠረበት የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱ ተጋጣሚዎች በተደጋጋሚ ወደ ግብ መድረስ ችለዋል። በ2ኛው ደቂቃ እንግዳዎቹ ኢትዮጽያ መድኖች በዮናታን ብርሃኑ የግብ ሙከራ በማድረግ የሀላባን የግብ ክልል መፈተሽ የጀመሩ ሲሆን 4ኛው ደቂቃ ላይ ምስግናው ወልደዮሐንስ ከርቀት የመታው ኳስ በግቡ በቀኝ አግዳሚ በወጣበት ቅፅበት ወደ ፊት የተጓዙት ሀላባዎች በምትኩ ማመጫ አማካይነት የግብ ሙከራ አድርገዋል። ቶሎ ቶሎ ወደ ፊት ይደርሱ የነበሩት ሀላባዎች 7ኛው ደቂቃ ላይ በምትኩ ማመጫ አማካይነት ያደረጉት ሌላ ሙከራም በግብ ጠባቂው የተመለሰ ሲሆን የመድን ተከላካይ በዛው ቅፅበት በእግሩ ኳስ አቀብሎ ግብ ጠባቂው በእጅ ይዟል በማለት ደጋፊዎች በመሀል ዳኛው ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አሰምተዋል።
ደቂቃዎች በጨመሩ ቁጥር የመድን የተከላካይ መስመር እየጠነከረ የመጣ ሲሆን የመሀል ክፍሉ ላይ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሳሙኤል በለጠም ኳሶችን ወደ ቀኝ እና ግራ መስመር በማሰራጨት የሀላባን የማጥቃት እንቅስቃሴ መግታት ችሏል። በኢትዮጽያ መድን በኩል ሳሙኤል በለጠ ሁለት ጊዜ እንዲሁም ምስጋናው ወልደሚካኤል ያደረጉትን የግብ ሙከራዋች የሀላባ ግብ ጠባቂ ሶፎንያስ ኑረዲን የግል ብቃት ታክሎባቸው ከግብነት ተርፈዋል። በሌላ በኩል ባለሜዳዋቹ ሀላባዋች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ቢደርሱም ኢላማውን የጠበቀ የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ ቀርተዋል ፤ ምትኩ ማመጫ እና ኤፍሬም ቶማስ ያገኟቸውን የግብ ዕድሎችም ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል። ጭማሪ ደቂቃ ላይ በተፈጠረው ክስተት ኢትዮጽያ መድኖች የማዕዛን ምት ሳይመቱ የማሀል ዳኛው ፊሺካ ሲያሰማ ውሳኔውን በመቃወም ሂደር ሙስጣፋ ከማሀል ዳኛው ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቷል። ነገር ግን በለገጣፎ ዋና አሰልጣኝ የነበረው ያሬድ ቶሌላ ወደ ሜዳ ዘሎ በመግባት ተጫዋቹን በማግባባት ከሜዳ ቢያስወጣውም ሂደር ሙስጠፋ ከራሱ የቡድን አጋር ዘሪሁን ብርሃኑ ጋር ግጭቱ ውስጥም ገብቶ ተስተውሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው የገቡት ሀላባዎች ወደ መድን የግብ ክልል ተጭነው ቢጫወቱም ግብ ማስቆጠር ግን ሳይችሉ ቀርተዋል። በተለይም 52ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ወንድሙ ፣ 60ኛው ደቂቃ ላይ ምትኩ ማመጫ እና 70ኛው ደቂቃ ላይ ካሳሁን ገረመው ባደረጓቸው ሙከራዎች ሀላባ ከተማን ቀዳሚ ለማድረግ ተቃርበው ነበር። በሌላ በኩል በ50ኛው ደቂቃ ምስጋናው ወልደሚካኤል እንዲሁም አብዱልለጢፍ ሙራድ ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጪ በመልሶ ማጥቃት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት መድኖች በግብ ሙከራ ከመጀመሪያው አጋማሽ ተቀዛቅዘው ታይተዋል።
75ኛው ደቂቃ ላይ የማዕዘን ምት ያገኙት ሀላባዎች ከማዕዘን ምት ያሻገሩት ኳስ በመድን ተከላካዮች ሲወጣ የሀላባ ተጫዋች በግብ ጠባቂው ተጠልፏል በሚል ቅሬታ ማሰማት የጀመሩ ሲሆን ደጋፊዎች የቡድን መሪያቸውን በመጥራት ክስ እንዲያስመዝግብ ጥረት በማድረጋቸው የዕለቱ ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ ክሱን ለመመዝገብ ወደ ዳር በሚመጣበት ወቅት ከደጋፊዎች በተወረወረ ድንጋይ ግንባሩ ላይ ተመቷል። አርቢትሩ ወድቆ ከፍተኛ ደም የፈሰሰው በመሆኑም በአምቡላንስ የህክምና እርዳታ ወደሚያገኝበት ቦታ ተወስዷል። ጨዋታውም በዚህ ምክንያት 76ኛው ደቂቃ ላይ ተቋርጧል።
በስፍራው ያናገርናቸው የሀላባ ክለብ አመራሮች በዛሬ ዕለት የተከሰተው ድርጊት በጣም አሳፋሪ እና አስነዋሪ መሆኑን ገልፀው ለፀቡ መነሳት ምክንያት ሆነዋል ያሏቸውን ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ገልፀዋል። ፌደራል ዳኛ ኤፍሬም ደበላ በሀላባ ሆስፒታል ህክምና ከተደረገለት በኋላ አሁን በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝም አረጋግጠናል።
በስፍራው ተገኝቶ የነበረው የሶከር ኢትዮጵያ ሪፖርተር ያነሳቸው ፎቶዎች እንዲሰረዙ በመደረጉ የጨዋታውን ሪፖርት በምስሎች ማስደገፍ አልተቻለም።
ወልቂጤ ከተማ ወደ ድሬዳዋ አምርቶ በሰፊ ጎል ልዩነት 7-1 አሸንፏል። ብስራት ታደሰ ሶስት ጎሎች በማስቆጠር ሐት-ትሪክ ሲሰራ አብዱልከሪም ወርቁ ሁለት ጎሎች አስቆጥሯል። ብስራት እና አህመድ ሁሴን ደግሞ በቀሪዎቹ ጎሎች ባለቤቶች ናቸው።
ዱራሜ ላይ ሀምበሪቾ ከአዲስ አበባ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ሲጠናቀቅ መድን ሜዳ ላይ ኢኮስኮ በመጨረሻው ደቂቃ በተቆጠሩት ጎል ከነጌሌ አርሲ ጋር 1-1 አቻ ተለያይተዋል። ዲላ ላይ በ8:00 የተደረገው የዲላ ከተማ እና ድሬዳዋ ፖሊስ ጨዋታም በተመሳሳይ 1-1 ሲጠናቀቅ ለድሬዳዋ ፖሊስ ዘርዓይ ገብረስላሴ፤ ለዲላ ኢብራሂም ቢያኖ ጎሎቹን አስቆጥረዋል። ሶዶ ላይ ወላይታ ሶዶ ከየካ ያለምንም የተጠናቀቀበት ጨዋታም የዛሬ መርሐ ግብር አካል ነበር።