በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት መቐለ 70 እንደርታ በሜዳው ሲዳማ ቡናን 3-1 ካሸነፈ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
” ሲዳማ ቡና በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኝ ቡድን በመሆኑ ጨዋታው ከባድ ነበር” – ገ/መድኅን ኃይሌ – መቐለ 70 እንደርታ
ስለ ጨዋታው
” ጨዋታው ከባድ ነበር፤ ሲዳማ ቡና በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኝ ቡድን ነው ፤ የያዙት ነጥብም ለዚህ ጨዋታ ጥሩ የስነልቦና ጥንካሬ አስገኝቶላቸዋል። በአንፃሩ እኛ አራት ጨዋታዎች ሳናሸንፍ ነው ወደ ጨዋታው የገባነው። በዚ ምክንያት ጨዋታው አክብዶብን ነበር። በአጠቃላይ ጨዋታውን አሸንፈናል። በቀጣይ ጨዋታዎች ቀስ በቀሰ ወደ አሸናፊነት መጥተን ይህን እናስቀጥላለን። ”
“ዳኝነት ላይ ያየሁት ነገር ጥሩ አይደለም” ዘርዓይ ሙሉ – ሲዳማ ቡና
ስለ ጨዋታው
” ከዕረፍት በፊት ከጨዋታ ውጪ ኳሱ በኋላ ተጫዋቾቻችን መረጋጋት አልቻሉም። በጨዋታው አሳፋሪ ዳኝነት ነው ያየሁት። ስለ ጨዋታው ብጠይቀኝ አሳፋሪ እና ሚዛናዊት የሌለው ዳኝነት ነው። የተቆጠርቡን ግቦች እኛ ላይ ጥፋት እየተፈፀሙ የተቆጠሩ ናቸው። ከጨዋታ ውጭ ሆኖም ግብ ይቆጠራል። በቃ ይህንን ነው ያየሁት። ከዚ ውጭ ግን መቐለ ለማሸነፍ የነበረው ተነሳሽነት ጥሩ ነበር። እንደ ቡድን ተንቀሳቅሰዋል እኛም የተሻለ ኳስ ተቆጣጥረን ተጫውተናል። እንዳያችሁት ኳሱን መስርተን ነው የወጣነው ግን በተለያዩ ስህተቶች ግብ ሲቆጠርብን የተጫዋቾቻችን ብቃት አወረደው። የምንፈልገው እንቅስቃሴ ያላደረግነው በዳኞች ምክንያት ነው። ገና በሰባተኛ ደቂቃ ነው የተጀመረው ይሄ ነገር። ጨዋታው ጥሩ ሆኖ ሳለ ሚዛኑ የጠበቀ ዳኝነት አላየንም። ዳኝነቱ ልክ ካልሆነ የጨዋታው እንቅስቃሴ እንዳለ ይበላሻል ይሄ ሁሉ ደጋፊ የገባው ጥሩ ጨዋታ ለማየት ነው። ለምንድነው ተጫዋቾች ሮጠው ዳኛ ላይ የሚሄዱት። በተደጋጋሚ ስህተት ይሰራ ነበር። እኛ ተጫዋቾቻችንን ብናረጋጋም የሚያደርጉት ስህተት ለሌላ ነገር የሚዳርግ ነበር። ዳኞቹ አቅም አንሷቸው ነው ብዬ አላስብም፤ ሆን ተብሎ የተደረገ ነገር ነው። ዳኝነት ላይ ያየሁት ነገር ጥሩ አይደለም። መቐለን ግን እንደ ቡድን ጥሩ ነው እንኳን ደስ አላቹ ማለት እፈልጋለው። ”
ስለ ስታድየሙ ድባብ
” ደጋፊው የሚደነቅ ደጋፊ ነው። በስርዓት ነው ቡድኑን የሚደግፈው። ምንም ነገር ቢፈጠር ቡድኑን ነበር ሲደግፍ የነበረው። ”
ዳኝነት ላይ ስለሰጠው አስተያየት
” እኔ አዳላ አላልኩም። ግን ብቃት ማነስ ነው ብዬ አላስብም። እነዚህ ሁሉ ግቦች እስኪቆጠሩ ብቃት ማነስ አይደለም። በአጠቃላይ ዳኝነቱ ሚዘናዊ አልነበረም። ሁሉም ግብ ላይ የዳኛ ተፅዕኖ አለበት፤ በቃ ይሄን ነው የምለው። አንዱን ከጨዋታ ውጪ ብለህ አንዱን የምታፀድቅ ከሆነ ስህተት ነው። “