ባሳለፍነው ሳምንት ከሁለት የውጪ ተጫዋቾቹ ጋር በስምሰምነት የተለያየው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋናዊው አጥቂ ሪቻርድ አርተርን ማስፈረሙን አስታውቋል።
የ25 ዓመቱ አጥቂ ሪቻርድ አርተር በኦል ስታርስ ከ2015 ጀምሮ የተጫወተ ሲሆን በ2016 ክለቡ የጋና ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን ሲሆን የቡድኑ አባል ነበር። ተጫዋቹ አምና ለግማሽ የውድድር ዓመት በውሰት ለአንጎላው ኢንተር ሉዋንዳ ሲጫወት ቀይቶ ወደ ኦል ስታርስ የተመለሰ ሲሆን ከስፔኑ ሁለተኛ ዲቪዝዮን ኮርዶባ እና የፈረንሳዩ ኦሊምፒክ ሊዮን ስለመዘዋወሩ በተለያዩ ወቅቶች በጋና መገናኛ ብዙሀን ተዘግቦለት ነበር።
በአጥቂ ስፍራ ላይ በርካታ አማራጭ ያለው ቅዱስ ጊዮርጊስ የአሌክስ ኦሮትማልን ስንብት ተከትሎ አርተርን በምትኩ በሁለት ዓመት ውል ያስፈረመ ሲሆን የተጫዋቹን ግልጋሎት የሚያገኘው ግን በመጋቢት ወር የሁለተኛው ዙር የሊግ ውድድር ሲጀምር ነው።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በመጠቀም ከአሌክስ ኦሮትማል ጋር አብሮ ባሰናበተው ካሰም ታይተስ ምትክ አደድ አማካይ ለማስፈረም የተቃረበ ሲሆን ምናልባትም የጎር ማሒያው ሐምፍሬይ ሚዬኖ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።