በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አስረኛ ሳምንት አዲስ አዳጊዎቹ እና በወራጅ ቀጠናው የሚገኙት ስሑል ሽረ እና ደቡብ ፖሊስን ሽረ ላይ ያገናኘው ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ሽረዎች ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ከተረታው ስብስባቸው አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ በሚድ ፎፋና ምትክ ልደቱ ለማን ሲጠቀሙ እንግዶቹ ደቡብ ፖሊሶች በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተሸነፈው ስብስባቸው መካከል ኤርሚያስ በላይ፣ ዘላለም ኢሳይያስ፣ ሙሉዓለም ረጋሳ እና ብሩክ ኤልያስን በማሳረፍ ዘሪሁን አንሼቦ፣ አዲስዓለም ደበበ፣ መስፍን ኪዳኔ እና የተሻ ግዛውን በመጠቀም ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ጨዋታው እንደተጀመረ ሁለቱም ቡድኖች ፈጣን የማጥቃስ እንቅስቃሴ እና ወደ ግብ ክልል የመድረስ አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉ ሲሆን ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ በማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ደቡብ ፖሊሶች ነበሩ። 4ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ ወገኔ ከአበባው ቡጣቆ የተሻማለትን ረጅም ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ ቢመታም ግብ ጠባቂው ሰንደይ ሮትሚ ሊያድንበት ችሏል። በሽረ ቡከል ደግሞ 10ኛው ደቂቃ ላይ ከግቡ በቅርብ ቦታ በኢብራሂም ፎፎና ላይ የተሰራውን ጥፋት በተገኘው ኳስ ጅላሎ ሻፊ ቅጣቱን አክርሮ ወደ ግብ ቢመታም ኳሱ በማንም ተጫዋች ሳይነካ ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቷል። ከተጋጣሚያቸው ብልጫ ወስደው የተጫወቱት ስሑል ሽረዎች ብዙም ሳይቆዩ ቀዳሚ የሆኑበትን ጎል አስቆጥረዋል። 14ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ልደቱ ለማ በእግሩ ጨርፎ በመምታት የመጀመርያውን ጎል ማስቆጠር ችሏል።
ከግብዋ መቆጠር በኋላ የደቡብ ፖሊስ ተጫዋቾች ሳይረበሹ በጥሩ ቅብብል በተደጋጋሚ ወደ ስሑል ሽረ ግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን በዚህም በ15ኛው ደቂቃ መስፍን ኪዳኔን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ኄኖክ አየለ በ26ኛው ደቂቃ ከተከላካዮች ነፃ ሆኖ በጥሩ አቋቋም ላይ ሆኖ ከበኃይሉ ወገኔ የተቀበለውን ኳስ በድንቅ አጨራረስ ወደ ግብነት በመቀየር ፖሊስን አቻ አድርጓል።
ጨዋታው በጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ተመልካቹን ሳቢ እግር ኳስ ያስመለከተ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ወደ መሪነት ለመሸጋገር ያቃረቧቸውን ሙከራዎችም ማድረግ ችለዋል። 33ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ዘላለም በረከት ኳሷ አየር ላይ እያለች ቀጥታ ወደ ግብ ቢመታም በደቡብ ፖሊስ ተከላካዮች ተጨርፋ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥታለች። በደቡብ ፖሊስ በኩል ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ኄኖክ አየለ 37ኛው ደቂቃ ላይ መሬት ለመሬት የተላከለትን ኳስ ተረጋግቶ ወደ ግብ ቢመታም ግብ ጠባቂው ሰንደይ አድኖበታል።
ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመርያው የተቀዛቀዘ እና በተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳት እየተቆራረጠ ፍሰት አልባ ሆኖ ተስተውሏል። በዚህ አጋማሽ ስሑል ሽረዎች የመጀመርያ ድላቸውን ለማግኘት ጫን ብለው ሲጫወቱ በአንፃሩ ደቡብ ፖሊሶች በማፈግፈግና ኳስን ወደ ኋላ በመመለስ አመዛኙን ጊዜ በራሳቸው የሜዳ ክፍል ሲቀባበሉ ተስተውለዋል።
ጨዋታ ወደ ፍፃሜው ባመራበት ሰዓት በኃይሉ ወገኔ በተከላካዮች ስህተት ያገኘውን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ የመታት ኳስ ወደ ውጪ የወጣበት አጋጣሚ ደቡብ ፖሊስ በመጨረሻ ድል ለማስመዝገብ እጅግ የተቃበረበበት ነበር። ጨዋታውም በመጀመርያ አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎች 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።