በኢትዮጵያ ረዘም ያለ ቆይታ ያላቸው ናይጄሪያዊያኑ አጥቂዎች ፊሊፕ ዳውዝ እና ላኪ ሰኒ ደቡብ ፖሊስን ተቀላቅለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የ2010 ቻምፒዮን በመሆን ከስምንት አመት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የተመለሰው ደቡብ ፖሊስ አጀማመሩ ጥሩ አይመስልም። በሊጉ ካደረጋቸው አስር መርሀ ግብሮች ደደቢትን በሜዳው ከመርታቱ ውጭ አብዛኛውን ጨዋታ በጠባብ ውጤት እየተሸነፈ በአምስት ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ 15ኛ ላይ ተቀምጧል፡፡ ቡድኑ በሜዳ ላይ ጥሩ የኳስ እንቅስቃሴን ያሳይ እንጂ ጨራሽ የሚባል የፊት አጥቂ ችግሩን በጉልህ ሲታይ ቆይቷል። ይህን ችግሩን ለመቅረፍም የውጪ ተጫዋቾች የዝውውር መስኮትን በመጠቀም የሊጉ ልምድ ያላቸው ፊሊፕ ዳውዝ እና ላኪ ሳኒን በአንድ ዓመት የውል ስምምነት ወደ ክለቡ መቀላቀሉን አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል ፡፡
በ2003 ለኤሌክትሪክ በመፈረም ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ፊሊፕ ዳውዝ በቀይ እና ነጭ ለባሾቹ ስኬታማ ጊዜያትን ካሳለፈ በኀላ በ2005 ወደ ደደቢት ቢያመራም የመሰለፍ እድል ባለማግኘቱ በግማሽ የውድድር ዓመት ወደ ንግድ ባንክ አምርቶ እስከ 2008 ድረስ በክለቡ ቆይቷል። በባንክ የመጨረሻ የውድድር ዘመኑ 19 ጎሎችን ያስቆጠረበትም በሊጉ ያሳለፈው ምርጡ ጊዜው ነበር። አጥቂው በ2009 ወደ ኩዌት እና ሳዑዲ አራቢያ ክለቦች አምርቶ ከተጫወተ በኋላ በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ባለፈው የውድድር ዓመት ለፋሲል ከነማ መጫወቱ የሚታወስ ነው።
ሌላኛው ደቡብ ፖሊስን የተቀላቀለው ናይጄርያዊ ላኪ ሳኒ በ2006 ለወልቂጤ ከተማ በመፈረም ነበር ወደ ኢትዮጵያ የመጣው። ቀጥሎ በጅማ አባ ቡና ጤሩ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ በ2008 ወደ ሲዳማ ቡና ያመራ ሲሆን ክለቡ በ2009 ለሊጉ ዋንጫ ሲፎካከር ወሳኝ ጎሎችን ማስቆጠር ችሎ ነበር። አጥቂው በ2010 ወደ አርባምንጭ ከተማ ቢያመራም ከግማሽ ዓመት በኋላ ክለቡን ለቆ እስከ ዓመቱ መጨረሻ በአዲስ አበባ ከተማ ቆይታ አድርጓል።
ከጋናዊው የመሐል ተከላካይ አዳሙ መሐመድ በመቀጠል የውጭ ተጫዋቾችን ቁጥር ወደ ከፍ ያደረገው ደቡብ ፖሊስ በግልፅ ሲታይ የነበረበትን የአጥቂ ክፍተት በሁለተኛው ዙር አዲስ ፈራሚዎችን ተጠቅሞ ይቀርፍ ይሆን የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ይሆኗል፡፡