የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የስምንተኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ጎንደር ዐፄ ፋሲለደስ ስታድየም ላይ ፋሲል ከነማ ደደቢትን አስተናግዶ 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ፋሲል ከነማ በኢትዮጵያ ዋንጫ ትግራይ ስታድየም ላይ ወልዋሎን 1-0 ካሸነፈው ስብስብ በርካታ ለውጦችን በማድረግ ነበር ወደሜዳ የገቡት ሽመክት ጉግሣ በአምስት ቢጫ ምክንያት በዛሬው ጨዋታ ባለመሰለፉ በእርሱ ምትክ ከተስፋ ቡድኑ ያደገው ዓለምብርሀን ይግዛው በሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የመሰለፍ እድል ሲያገኝ ሰዒድ ሁሴን፣ ሐብታሙ ተከስተ፣ ኤዲ ቤንጃሚን፣ ዮሴፍ ዳሙዬ እንዲሁም ግብ ጠባቂ ቴዎድሮስ ጌትነትን (በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ) የመጀመሪያ ተሰላፊ አድርገው ነበር ወደ ሜዳ የገቡት። በደደቢት በኩል ባህር ዳር ላይ በባህርዳር ከተማ 2-0 ከተሸነፈው ስብሰብ በኤፍሬም ጌታቸው ምትክ ዳዊት ወርቁን፤ በአክዌር ቻም ደግሞ ሙሉጌታ ብርሀነ በመተካት ነበር ወደሜዳ የገቡት።
የመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ተጭነው መንቀሳቀስ የቻሉት ባለሜዳዎቹ ጎል ለማግኘት ብዙ ደቂቃ አላስፈለጋቸውም። 8ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ኤዲ ቤንጃሚን ወደ ግብ ያሻማው ኳስ በደደቢት ተከላካዮች ተገጭቶ ሲመልስ ሙጂብ ቃሲም አግኝቶ ወደግብ በመቀየር ፋሲልን ቀዳሚ አድርጓል።
አጼዎቹ ከግቡ በኋላ በተሻለ ሁኔታ ተጭነው መጫወታቸውን በመቀጠል 13ኛው ደቂቃ ላይ ከመሐል ሜዳ ዮሴፍ ዳሙዬ በጥሩ ሁኔታ ይዞ ከመጣ በኋላ ለኤዲ ቤንጃሚን አቀብሎት ኤዲ ቤንጃሚን ለኤፍሬም ዓለሙ ቢያመቻችለትም ኤፍሬም ሁለት ተካላካዮች አልፎ ያመከነው ኳስ በመጀመሪያው አጋማሽ የሚያሰቆጭ አጋጣሚ ነበር። 17ኛ ደቂቃ ላይ ከሱራፌል ዳኛቸው የተሻገረለትን ኳስ ዓለምብርሀን ይግዛው ወደግብ አክርሮ የመታው ኳስ ኢላማውን ያልጠበቀው ሌላ የሚጠቀስ አጋጣሚ ነበር።
27ኛ ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው በመጎዳቱ ተክቶት ወደ ሜዳ የገባው በዛብህ መለዮ ወደ ጨዋታው ቅኝት ለመግባት በመቸገሩ የፋሲል ከነማን የማሐል ሜዳ ብልጫ ተቋቁመው ወደ ጨዋታ የተመለሱት ደደቢቶች ጨዋታው ግማሽ ሰዓት ካስቆጠረ በኋላ የግበ ዕድል መፍጠር ጀምረዋል። 33ኛ ደቂቃ ዓለምአንተ ካሳ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኝውን የቅጣት ምት እንዳለ ከበደ ወደግብ አክርሮ የመታው እና ግብ ጠባቂ የመለሰበት፣ በድጋሚ 36ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ዳግማዊ ዓባይ ሙጅብ ቃሲምን አልፎ ወደግብ አክርሮ መትቶ ግብጠባቂው ያዳነበት
በደደቢት በኩል በመጀመሪያው አጋማሽ የሚጠቀሱ ነበሩ።
43ኛ ደቂቃ ላይ ዓለምብርሀን ይግዛው ከመሀል ወደቀኝ መስመር የጣለለትን ኳስ ዮሴፍ ዳሙዬ በቀኝ መስመር ሁለት ተከላካዮችን አልፎ ወደ ግብ አጥብቦ በመግባት ወደግብ የመታዉ ኳስ ግብ ጠባቂው ሲመልሰው ኤዲ ቤንጃሚን ደርሶ ወደ ግብ በመቀየር ባለሜዳዎቹ 2-0 እየመሩ ወደ እረፍት አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የደደቢት ብልጫ የታየበትና እንቅስቃሴ መሐል ሜዳ ላይ ያተኮረ ነበር። 53ኛው ደቂቃ ላይ በዛብህ መለዮ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ በተከላካዮች ተገጭቶ ሲመለስ ሐብታሙ ተከስተ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ያመከነው በሁለተኛው አጋማሽ በፋሲል በኩል የሚጠቀስ ሙከራ ነበር። 62ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በመጠቀም ከግብ ጠባቂው ጋር የተገናኘው እንዳለ ከበደ አጋጣሚውን ወደ ግብነት በመቀየር ደደቢቶች የተሻለ ተጭነው ለመጫወት መነቃቃት የፈጠረላቸውን እና ልዩነቱን ማጥበብ ያስቻላቸውን ግብ አስቆጥሯል።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ፋሲሎች የአጥቂ ክፍላቸውን ለማጠናከር ኤፍሬም ዓለሙን በማስወጣት ኢዙ አዙካን አስገብተው ግብ የማግባት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። ካደረጓቸው ሙከራዎች መካከልም 68ኛው ደቂቃ ላይ ኢዙ አዙካ ከኤዲ ቤንጃሚን ተቀብሎ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ሲድንበት 75ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በቀኝ መስመር ከሰዒድ ሁሴን የተሻገረለትን ኳስ ኤዲ ቤንጃሚን በጭንቅላቱ ቢገጨውም ኢላማውን ሰይጠብቅ ቀርቷል።
በደደቢቶች በኩል 77ኛው ደቂቃ ላይ የዓብስራ ተስፋዬ ከዮሴፍ ዳሙዬ የነጠቀውን ኳስ ወደ ቀኝ መስመር አሻምቶ አሌክሳንደር ዐወት ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ወደ ግብ ሲሞክር ከኋላ ደርሶ ኳሱን ያዳነው ሙጁብ ቃሲም ተጎድቶ ከሜዳ ወጥቷል። ሙጂብ ጉዳቱ ከፍተኛ በመሆኑም ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።
ጨዋታው በፋሲል ከነማ 2-1 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ ዐፄዎቹ ደረጃቸውን ወደ 4ኛ ሲያሻሽሉ ደደቢት በአንፃሩ በደረጃ ሰንጠረዙ መጨረሻ ላይ እንደተቀመጠ ቀርቷል።