በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ወደ ሞቃታማዋ ድሬዳዋ ያመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሳላዲን ሰዒድ ብቸኛ ግብ 1-0 በማሸነፍ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ለመገናኛ ብዙሀን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
” በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለን ቀርበናል ” ስቴዋርት ሃል – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ስለ ጨዋታው
“ተጋጣሚያችን በጣም ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል። የመጫወቻ ሜዳው ፍፁም ምቹ አልነበረም፤ እነሱ በየቀኑ ልምምድ ስለሚሰሩበት የሜዳውን ባህሪ በደንብ ተረድተው ነው የሚጫወቱት፡፡ እኛ ጨዋታውን ስንጀምር ጥሩ አልነበርንም፤ ጨዋታውን ስንጀምር ምንም አይነት ጉልበት (energy) አልነበረንም። ይህም ተጋጣሚያችንን ኳሶችን እንዳይመሰርቱ ኳሱን እንዳይቆጣጠሩ በማድረጉ በኩል ደካማ እንድንሆን አድርጎናል፡፡በዚህም የተነሳ እነሱ በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ እንዲንቀሳቀሱ አድርጓቸዋል። ነገርግን በመከላከሉ ረገድ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ነበርን።
” በሁለተኛው አጋማሽ በራሳችን ደስተኛ አልነበርንም። በእረፍት ሰአት በግልፅነት ተወያይተናል በዚህም በመጀመሪያው አጋማሽ የአቅማቸውን ሰጥተው እየተጫወቱ ያልነበሩ የተወሰኑ ተጫዋቾች እንዲያሻሽሉ ተመካክርን ነበር ወደ ሁለተኛው አጋማሽ የገባነው፡፡ በዚህም ተሻሽለን ቀርበናል፤ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ ከራሳቸው ሜዳ መስርተው እንዳይወጡና ግብ ጠባቂያቸው ረጃጅም ኳሶችን እንዲለጋ በማድረግ ችለናል። በሁለተኛው አጋማሽ በሜዳው የላይኛው ክፍል ላይ ጫና ፈጥረን መጫወት ችለናል፡፡
” ሳላዲን ሁሌም ሳላዲን ነው ፤ እሱ የተለየ ነው። ኳሱን ሳጥን ውስጥ ካገኘ ምህረት የለውም፡፡”
“90 ደቂቃ የተሻልክ ሆነህ ተሸንፈህ ስትወጣ ያበሳጫል” ስምዖን ዓባይ – ድሬዳዋ ከተማ
ስለ ጨዋታው
“እግርኳስን አስደሳች የሚያረጉት እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች ናቸው። ለአሸናፊው ቡድን በተለይ 90 ደቂቃ ብልጫ ተወስዶብህ ሶስት ነጥብ ይዘህ መውጣት ስትችል ደስ ይልሀል። በአንጻሩ ደግሞ 90 ደቂቃ የተሻልክ ሆነህ ተሸንፈህ ስትወጣ ያበሳጫል፡፡ ጨዋታው ያስተማረን ነገር ቢኖር 90 ደቂቃ የተሻልክ ብትሆንም ፊሽካ ሲነፋ በውጤት ካልታጀበ ዋጋ እንደሌለው አስተምሮን አልፏል፡፡ በጨዋታው በእንቅስቃሴ ደረጃ የተሻልን ብንሆንም እንደቡድን ብዙ ማስተካከል ያሉብን ነገሮች አሉ። በውጤቱ ብንከፋም በተጫዋቾች መካከል ከነበረው የጥራት ልዩነትና እኛ ካለን የቡድን ስብስብ አንጻር ውጤቱ ብዙም የሚያስገርም አይደለም፡፡”
ቡድኑ ስላለበት የፈጣሪ አማካይ ችግርና የመሀል ተከላካይ ተሰላፊዎች በቁመት አጭር ስለመሆን
“እግርኳስ ምንም የሚደበቅ ነገር የለውም። ሁሉም ነገር ሜዳ ላይ የሚታይ ነው። በመሀል ተከላካይ ስፍራ የምናጣምራቸው ሁለቱም ተጫዋቾች ልምድ ያላቸው ናቸው። ምንም እንኳን በቁመታቸው አጠር ያሉ ቢሆንም በጨዋታው የአየር ላይ ኳስ አጠቃቀም ላይ ጥሩ በሆኑት ሳላዲን ሰዒድና ጌታነሀ ብዙም ብልጫ አልተወሰደባቸውም። ለመሀል ተከላካይ ተጫዋች የቁመት ጉዳይ ሳይሆን ወሳኙ በትኩረት መጫወት ነው፡፡ በሁለቱ ጨዋታዎች በተመሳሳይ በመጨረሻ ደቂቃ ግብ ማስተናገዳችን ተጫዋቾቹ በአዕምሯቸው ላይ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ነው፡፡
” በነበሩን የመጀመሪያ ተሰላፊ አማካዮች ጨዋታው ለረጅም ደቂቃ ለመቀጠል የተገደድነው ተጠባባቂ ወንበር ላይ ፈጣሪ አማካዮች የሉንም፤ በብዛት የመከላከል ባህሪ ያላቸው የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች ነው ያሉን። በቀጣይም ምን እንደሚፈጠር ባናውቅም መስተካከል የሚገባው ነገር እንደሆነ ግን አምናለሁ፡፡”