በደደቢት እና አዳማ ከተማ መካከል የሚደረገውን የ11ኛው ሳምንት የነገ መርሐ ግብር የተመለከቱ ነጥቦችን እንደሚከተለው እናስነብባችኋለን።
በሊጉ ግርጌ የተቀመጠው ደደቢት መነቃቃት እያሳየ የሚገኘው አዳማ ከተማን የሚያስተናግድበት ብቸኛው የነገ ጨዋታ 09፡00 ላይ በትግራይ ስታድየም ይጀምራል። ሜዳው ላይ ባደረገው የመጨረሻ ጨዋታ ወላይታ ድቻን ማሸነፍ ችሎ የነበረው ደደቢት በባህር ዳር እና ፋሲል የደረሰበት ተከታታይ ሽንፈት ካለበት የመጨረሻ ደረጃ እንዳይንቀሳቀስ አድርጎታል። ከበላዩ ያሉት ክለቦች በነጥብ አለመራቅ ግን ደደቢት ከዚህ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ አግኝቶ መጠነኛ እፎይታን ለማግኘት እንዲያልም የሚያደርጋው ነው። በተቃራኒው ምንም እንኳን 9ኛ ደረጃ ላይ ቢቀመጥም አዳማ ከተማ መልካም ጊዜን እያሳለፈ ይገኛል። ከደካማ አጀማመራቸው በተለየ ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎችን ማሸነፍ የቻሉት አዳማዎች አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እያላቸው እስከ አምስተኛነት ከፍ የማለት ተስፋን ይዘው ነው ወደ መቐለ ያመሩት።
ደደቢት ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ የሆነ ሙሉ ስብስቡን ይዞ ለነገው ጨዋታ ሲደርስ በአዳማ በከል ግን በጉዳት ወደ መቐለ ያልተጓዙ ተጫዋቾች አሉ ፤ ከንዓን ማርክነህ ፣ ሱራፌል ጌታቸው ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ እና አንዳርጋቸው ይላቅ በዚህ ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።
እርስ በእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ደደቢት እና አዳማ ከተማ በሊጉ ከተገናኙባቸው 16 ጨዋታዎች ውስጥ 31 ግቦች ያስቆጠረው ደደቢት 8 ጨዋታዎችን በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን አዳማ ከተማ 5 ጊዜ አሸንፎ 15 ግቦችን አስቆጥሯል። ቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ነበሩ።
– የእርስ በእርስ ግንኙነቱ በርካታ ጎሎች (46) የተቆጠሩበት ሲሆን ደደቢት በሁለት አጋጣሚዎች (6-1 እና 7-1) ያሸነፈባቸው ውጤቶች ለጎሎቹ መጠን መጨመር እንደምክንያት የሚጠቀስ ነው።
– በሜዳው አራት ጨዋታዎችን ያደረገው ደደቢት በሦስቱ ሽንፈት ገጥሞት በአንዱ ድል ቀንቶታል። አምስት ግቦች ሲቆጠሩበትም አንድ ግብ ብቻ ቀንቶታል።
– አራት የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ያደረገው አዳማ በሁለቱ ሲሸነፍ አንድ ድል አስመዝግቦ አንዴ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
ዳኛ
– ጨዋታውን ፌደራል ዳኛ አዳነ ወርቁ ይመራዋል። አርቢትሩ እስካሁን ሁለት ጨዋታዎችን ዳኝቶ ስምንት የቢጫ ካርዶችን መዟል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ደደቢት (4-2-3-1)
ረሺድ ማታውሲ
መድሀኔ ብርሀኔ – ኤፍሬም ጌታቸው – ክዌኪ አንዶህ – ኄኖክ መርሹ
አብርሀም ታምራት – የአብስራ ተስፋዬ
ዳግማዊ ዓባይ – ዓለምአንተ ካሳ – አቤል እንዳለ
አኩዌር ቻሞ
አዳማ ከተማ (4-2-2)
ሮበርት ኦዶንካራ
ሱራፌል ዳንኤል – ምኞት ደበበ – ተስፋዬ በቀለ – ሱለይማን መሀመድ
ቡልቻ ሹራ –አዲስ ህንፃ – ኢስማኤል ሳንጋሪ – በረከት ደስታ
ሙሉቀን ታሪኩ – ዳዋ ሁቴሳ