በ12ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባህር ዳር ከተማ ከ ፋሲል ከነማ ያደረጉት ጨዋታ ያለጎል ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ወደ ግብ አለመቀየራችን ቢያስቆጭም በጨዋታው ደስተኛ ነኝ” ጳውሎስ ጌታቸው – ባህር ዳር ከተማ
ስለ ጨዋታው
“ጨዋታው ውጥረት የነበረበት ነበር። ሁለታችንም አሰልጣኞች ኳስ የሚጫወት ቡድን ስለገነባን ኳስ ላይ የተመሰረተ ጨዋታ ነው የተጫወትነው። ተጨዋቾቼ ሙሉ 90 ደቂቃ የሚፈለገውን ዋጋ ከፍለው ተንቀሳቅሰዋል። ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ወደ ግብ አለመቀየራችን ቢያስቆጭም በጨዋታው ደስተኛ ነኝ። በጨዋታው የሚፈለገውን ለሰጡት ተጨዋቾቼ ግን ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለው”
ስለ ሁለተኛው አጋማሽ ጥንካሬያቸው
“በሁለተኛው አጋማሽ እድል ከእኛ ጋር አልነበረችም። ያገኘናቸውን ሁለት ሶስት አጋጣሚዎች ወደ ጎልነት አለመቀየራችን ቢያስቆጭም ተጨዋቾቼ ባደረጉት ነገር ደስተኛ ነኝ። በመጀመሪያው አጋማሽ አስበን የገባነው በመሐል ሜዳ ላይ እነሱን በልጠን ለመጫወት ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ይህንን ነገር አጠናክረን በመግባት ብዙ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን ፈጥረናል፤ ነገር ግን አልተሳካም።”
ስለ ደርቢነት ስሜት
“በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ባህር ዳር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ከፋሲል ከነማ ጋር የተገናኘው፤ ይህ የደርቢነት ስሜት ደግሞ በጣም ደስ ይላል። በጨዋታው ደስተኛ ነኝ። ይህ የወንድማማቾች ደርቢ ደግሞ ጥሩ ስሜት አለው። እኛም በመልሱ ጨዋታ ወደ ጎንደር ተጉዘን የተቻለንን ለማድረግ እና ይህንን ደርቢ ለማሳመር እንሞክራለን።”
ስለ አጥቂ መስመራቸው የአጨራረስ ችግር
“እኔ የሚያሳስበኝ ጎል ጋር የመድረሳችን ሂደት ነው። እኛ ዛሬ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚያችን የግብ ክልል እንደርስ ነበር። ተጫዋቾቼ ደጋፊውን ለማስደሰት በጣም ጓጉተው ስለነበር ነው የተገኙትን አጋጣሚዎች ወደ ግብነት መቀየር ያልቻሉት። ለቀጣይ ግን እነዚህን የአጨራረስ ክፍተቶች አስተካክለን ለመቅረብ እንሞክራለን።”
ስለ ቀጣይ ጨዋታዎች እና እቅዳቸው
“በቀጣይ ሁለት ተከታታይ የሜዳችን ውጪ ጨዋታዎች አሉብን። እነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ደግሞ የምናደርገው በጠባብ ጊዜ ውስጥ ነው። ይህንን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ቢያጤነው ጥሩ ነው። እኛ በተቻለን መጠን ከጉዞ እና ከጨዋታ መደራረቦች ጋር ያሉብንን ችግሮች እያቻቻልን ልምምዶችን ሰርተን ለየጨዋታዎቹ እንቀርባለን። እኛ ገና ዘንድሮ ነው ወደ ሊጉ ያደግነው። ከእኛ ጋር ያደጉትን ክለቦች መመልከት ትችላላችሁ፤ ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ። እኛ ግን ዋንጫ ፉክክር ውስጥ ነን። አትጠራጠሩ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ጥሩ ነገር ይዘን እንጨርሳለን።
“የሁለታችንም አጨዋወት ክፍት ስለነበረና ሙከራዎች ስለነበሩት መልካም ጨዋታ ነበር” ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ
ስለ ጨዋታው
“ጨዋታው ለእኔ ደስ የሚል ነበር። በሁለቱም ቡድኖች በኩል የነበረው አጨዋወት ክፍት ስለነበር እና ሙከራዎች ስለነበሩት መልካም ጨዋታ ነበር። ብዙ ደጋፊዎችም ጨዋታውን ለማየት ስታዲየም ስለገቡ ጥሩ ጨዋታ ማየት ስላለባቸው ሁለታችንም ጥሩ ተንቀሳቅሰናል።”
በሁለተኛው አጋማሽ ስለተወሰደባቸው ብልጫ
“በሁለተኛው አጋማሽ ጥንቃቄን መርጠን ተጫውተናል። ይህ ደግሞ የሆነው ከሜዳችን ውጪ ስለተጫወትን ነው። ነገር ግን ይህ ማለት ሙሉ ለሙሉ ተከላክለን መጫወትን ፈልገን ነው የገባነው ማለት አይደለም። ብልጫም እንዲወሰድብን የሆነው የተከላካይ ክፍላችን ብቻውን ተነጥሎ ወደ ኋላ በመምጣቱ እና ከመሐል ሜዳ እንዲሁም ከአጥቂ መስመር ክፍሉ ጋር የነበረው ክፍተት በመስፋቱ ነው።”