በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ወደ መቐለ ያመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወልዋሎን 1-0 በማሸነፍ አምስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቦ የመሪነት ስፍራው ላይ ተቀምጧል።
ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች ባለፈው ሳምንት በአዳማ ሽንፈት ከገጠመው ስብስባቸው አፈወርቅ ኃይሉን (ቀይ ካርድ) በሪችሞንድ አዶንጎ ቀይረው ሲገቡ ፈረሰኞቹ በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት ደደቢትን ካሸነፈው ስብስባቸው ሰልሃዲን በርጌቾን (ጉዳት) በምንተስኖት አዳነ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ባለፈው ሳምንት ድንገተኛ አደጋ አጋጥሟቸው ህይወታቸውን ላጡት የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች በተደረገው የህሊና ፀሎት የጀመረው ጨዋታው ሳቢ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የታየበት አልነበረም። በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ ጫና ፈጥረው የተጫወቱት ባለሜዳዎቹ ወልዋሎዎች በተለይም በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር። ሪችሞንድ አዶንጎ ከፕሪንስ የተሻማውን የቅጣት ምት ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ እና አማኑኤል ጎበና እና ሪችሞንድ አዶንጎ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን ገብተው አማኑኤል አክርሮ መትቶ ፓትሪክ ማታሲ ያዳናት ይጠቀሳሉ። እንደተለመደው በመስመር ላይ በሚደረጉ ፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች ለማጥቃት የሞከሩት ቢጫ ለባሾቹ ከላይ ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም በብርሃኑ አሻሞ እና ፕሪንስ ሰቨሪንሆ አማካኝነት ከርቀት ሙከራ አድርገው ነበር።
ከተጋጣምያቸው ወልዋሎ በተለየ ለአጥቂዎቻቸው በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች ለማጥቃት የሞከሩት ፈረሰኞቹ ምንም እንኳ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ጥቂት ግን ንፁህ የግብ ዕድል ፈጥረዋል። ሳላዲን ሰዒድ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው እጅግ በሚያስደንቅ ብቃት ሲያወጣው ታደለ መንገሻ በጥሩ ሁኔታ ገብቶ ያደረገው ሙከራ በተመሳሳይ መንገድ በጊኒያዊው ግብጠባቂ አብዱላዚዝ ግብ ከመሆን ተርፏል። በጨዋታው ያገኟቸውን ጥቂት ዕድሎች ወደ ግብ ለመቀየር ጥረት ሲያደርጉ የታዩት ጊዮርጊሶች ከላይ ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጪ በሳላዲን ሰዒድም ጥሩ ሙከራ አድርገው ነበር።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሁሉም ረገድ ተሽለው የታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ ወሳኝ ተጫዋቻቸው ኤፍሬም አሻሞን በጉዳት ቀይረው ያስወጡት ወልዋሎዎች ከመጀመርያው አጋማሽ የወረደ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በአንፃሩ ፈረሰኞቹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ከመውሰድ አልፈው በርካታ ሙከራዎች ያደረጉበት ነበር። አጋማሹ ከተጀመረ ጀምሮ ጫና ፈጥረው ለመጫወት የሞከሩት ጊዮርጊሶች በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች ሶስት እጅግ ለጎል የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም ጌታነህ ከበደ ከመስመር አሻምቷት ነፃ አቋቋም ብቻውን የነበረው ሰልሃዲን ሰዒድ በግንባሩ ገጭቶ ያመከናት ወርቃማ ዕድል እና ታደለ መንገሻ ከሳጥኑ ጠርዝ መቷት አብዱልዓዚዝ ኬይታ በግሩም ሁኔታ ያወጣት ፈረሰኞቹን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ነበሩ። በ65ኛው ደቂቃ ላይም ሳላዲን ሰዒድ ከጌታነህ ከበደ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ግሩም ግብ በማስቆጠር ቡድናቸው ለመደገፍ ረጅም ርቀት ተጉዘው የመጡትን ደጋፊዎች አስፈንድቋል።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የተሻለ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተጠግተው የተጫወቱት ወልዋሎዎች ምንም እንኳ አቻ የሚሆኑበትን ግብ ባያገኙም በፕሪንስ ሰቨሪንሆ እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች አድርገው ነበር። አማካዩ አክርሮ መትቶ ፓትሪክ ማታሲ እጅግ በሚያስደንቅ ብቃት ያዳነው ሙከራ እና ብዙም ሳይቆይ የተከላካዮች ስህተትን ተጠቅሞ ያደረገው ሙከራ ባለሜዳዎቹ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት የተቃረቡባቸው ሙከራዎች ነበሩ።
በጨዋታው የብቸኛ ግቧ ባለቤት ሳላዲን ሰዒድ ከዕረፍት በፊት እና ከዕረፍት በኃላ የተለያየ የማልያ ቁጥር ለብሶ መጫወቱ እና የወልዋሎው ጊኒያዊ ግብ ጠባቂ አብዱልዓዚዝ ኬታ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ ያሳየው መራር የሃዘን አገላለፅ የብዙዎችን ትኩረት የሳቡ ክስተቶች ነበሩ።