በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሐ ስምንተኛ ሳምንት ስድስቱም ጨዋታዎች እሁድ ሲከናወኑ ሀዲያ ሆሳዕና፣ አርባምንጭ ከተማ ከፋ ቡና እና ነቀምት ከተማ ተጋጣሚያዎቻቸውን አሸንፈዋል።
ሻሸመኔ ላይ ሻሸመኔ ከተማ ከጅማ አባ ቡና ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል አቻ ተጠናቋል። ፈጣን እንቅስቃሴ ታይቶበት የነበረው የሻሸመኔ እና የጅማ አባቡና ጨዋታ ቀስ በቀስ ኃይል ወደተቀላቀለበት አጨዋወት ተለውጧል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዋች ሁለቱም ቡድኖች ወደ ፊት በመሳብ የተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል ለመፈተሽ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በተለይም በ8ኛው ደቂቃ ላይ የግብ ጠባቂው ሲሳይ ባንጫ ስህተትን ታክሎበት የመጀመሪያ የግብ ሙከራ ማድረግ የቻለው የጅማው ካርሎስ ዳምጠው ያደረገው ሙከራ በራሱ በግብ ጠባቂው ከሽፎበታል።
ቀስ በቀስ ጅማ አባ ቡና ወደፊት መሳቡን በማቆም በራሱ የሜዳ ክፍል ሲገደብ ባለሜዳው ሻሸመኔም ወደፊት የሚደርጉት እንቅስቃሴ ቶሎ ቶሎ የሚቆራረጥ ነበር። በሻሸመኔ በኩል ሙሉቀን ተሾመ፣ አብርሃም ዓለሙ እና አብዱልፈታ ከድር ያደረጉት የግብ ሙከራ ተጠቃሽ ነበር።
በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሻሸመኔ ሙሉ ለሙሉ በተጋጣሚያቸው ሜዳ ክፍል በማመዘን እድል ቢፈጥሩም ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በተለይም በ67ኛው እንዲሁም 76ኛው ደቂቃ አባባየው ስጦታው እና ጌታለም ማሙዬ ያደረጉት የግብ ሙከራወረች በግቡ አግዳሚ ታከው የወጡባቸው አጋጣሚዎች አስቆጪ ነበሩ። በጅማ አባ ቡና በኩል በግዝፉ አጥቂያቸው ካርሎስ ዳምጠው በመልሶ ማጥቃት ሲያደርጉት የነበረው ጥረት ብዙም ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል። ጨዋታውም ያለ ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ሆሳዕና ላይ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭን ያስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና 5-1 አሸንፎ መሪነቱን አጠናክሯል። አንጋፋው ኬንያዊ አጥቂ ኤሪክ ሙራንዳ ሐት-ትሪክ በመስራት በደመቀበት ጨዋታ በ21ኛው እና 36ኛው ደቂቃ በኤሪክ ጎሎች 2-0 እየመሩ የመጀመርያው አጋማሽ ተጠናቋል። ከዕረፍት መልስ ዳግም በቀለ 57ኛው ደቂቃ ላይ ልዩነቱን ወደ ሶስት ከፍ ማድረግ ሲችል በ72ኛው ደቂቃ ኤሪክ ሙራንዳ ለራሱ ሶስተኛ ለቡድኑ አራተኛ ጎል ባስቆጠረበት ቅፅበት የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል የዕለቱን ረዳት ዳኛ ታምሩ ኳስ ከጨዋታ ውጭ ነው በማለት ውዝግብ ውስጥ የገቡ ሲሆን የእለቱ ዋና ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ አሰልጣኙን ከሜዳ እንዲወጣ በማድረግ ጨዋታው ከ16 ደቂቃዎች በኋላ ሊቀጥል ችሏል።
ጨዋታው ቀጥሎ በ83 ኛው ደቂቃ የሆሳናው ተከላካይ ትዕግስቱ አበራ ኳስ በግብ ክልል ውስጥ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ወደ ግብ በመለውጥ ውጤቱን 4-1 ማድረግ ቢችሉም በተጨማሪ ደቂቃ ትዕግስቱ አበራ አምሰትኛ ጎል አስቆሮ በሆሳዕና 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ወደ ቦረና ያቀናው አርባምንጭ ከተማ ነጌሌ ቦረናን 3-2 ማሸነፍ ችሏል። አርባምንጭ ድል እንዲያስመዘግብ የረዳቸውን ጎሎች ማስቆጠር የቻሉት አለልኝ አዘነ አቦነህ ገነቱ እና ስንታየሁ መንግስቱ ናቸው።
ነቀምት ላይ ነቀምት ከተማ አዲስ አዳጊው ሺንሺቾን አስተናግዶ 2-1 ማሸነፍ ችሏል። በ37ኛው ደቂቃ ብሩክ ብርሃኑ፤ በ68ኛው ደቂቃ ዳንኤል ዳዊት በ68ኛው ደቂቃ የማሸነፍያ ጎሎችን ያስቆጠሩ ተጫዋቹች ናቸው።
ቦንጋ ላይ ካፋ ቡናን ቤንች ማጂ ቡና ያገናኘው ጨዋታ በካፋ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ምንተስኖት በ49ኛው ደቂቃ ብቸኛዋን የድል ጎል አስቆጥሯል።
ወደ ቡታጅራ ያመራው ስልጤ ወራቤ ቡታጅራ ከተማን 1-0 ያሸነፈበት ጨዋታም በዚህ ሳምንት የተካሄደ ሌላው ጨዋታ ነው።