ከዛሬ የ13ኛው ሳምንት ጨዋታዎች ውስጥ ወላይታ ድቻ እና ባህር ዳር ከተማ በሚገናኙበት ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ሀሳቦች አንስተናል።
የጦና ንቦቹ የጣና ሞገዶቹን በሶዶ ስታድየም የሚያስተናገዱበት የ13ኛ ሳምንት ጨዋታ ረፋድ 09፡00 ላይ ይጀምራል። ከስድስተኛው ሳምንት በኋላ በስድስት ጨዋታዎች ሦስት ነጥብ ማስካት እየተሳናቸው ከሜዳ ሲወጡ የሰነበቱት ወላይታ ድቻዎች እስካሁን ሽንፈት ወዳላስተናገዱበት ሜዳቸው ይመለሳሉ። ቡድኑ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ወደ ጎንደር እና ጅማ ባደረጋቸው ጉዞዎች ተከታታይ ሽንፈት አስተናግዶ ነው ዛሬ ባህር ዳርን የሚያስተናግደው። ወላይታ ድቻ ወረጃ ቀጠና ውስጥ ከሚገኙ ቡድኖች አንፃር ሲታይ ከአንድ ጨዋታ ውጤት ያነሰ ርቀት ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ ከዛሬው ጨዋታ ውጤት ለማስመዝገብ በሙሉ ኃይሉ በማጥቃት ላይ ተመስርቶ ወደ ሜዳ እንደሚገባም ይጠበቃል። ምንም እንኳን አማካዮቹ ፍፁም ተፈሪ እና እዮብ ዓለማየሁ በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ስብስብ ውጪ ቢሆኑም ለረጅም ጊዜ በጉዳት የቆየው ኃይማኖት ወርቁ ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ አገግሞ የተመለሰ መሆኑ እና የመስመር ተከላካዩ እሸቱ መናም የአራት ጨዋታዎች ቅጣቱን መጨረሱ ለጦና ንቦቹ መልካም ዜና ሆኗል።
አስራ ስድስት ነጥቦችን ይዘው በሊጉ ወገብ የተቀመጡት ባህር ዳር ከተማዎች እስከ ሰባተኛው ሳምንት ያሳዩት ግስጋሴ እየራቃቸው ይገኛል። ከመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎቻቸው በአማካይ አንድ ነጥብ እያገኙ መቀጠላቸውም ከዋንጫ ፉክክሩ እንዲርቁ አድርጓቸዋል። በርግጥ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ያሏቸው መሆኑ ከበላያቸው እንዳሉ በርካታ ክለቦች ሁሉ ደረጃቸውን ለማሻሻል ተስፋ የሚሰጣቸው ነው። ደደቢትን ካሸነፉበት ጨዋታ በኋላ በወልዋሎ ሽንፈት ሲገጥማቸውም ሆነ ከፋሲል ነጥብ ሲጋሩ ኳስ እና መረብን ማገናኘት አለመቻላቸው ግን ከዚያ እስቀድሞ በሀዋሳው ጨዋታ ላይ ብቻ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ለወጡት ባህር ዳሮች እንደ ድክመት የሚነሳ ነው። በመሆኑም ቡድኑ በእስካሁኑ ጉዞው በአመዛኙ ግብ የማስቆጠር ኃላፊነቱን እየወሰዱ ከሚገኙት አጥቂዎቹ ውጪም ከሌሎቹ ተሰላፊዎችም ግቦችን ማግኘት ይጠበቅበታል። ሆኖም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ቡድኑን ማገልገል ያልቻለው አማካዩ ዳንኤል ኃይሉ ለዛሬው ጨዋታ የማይደርስ ሲሆን በሳምንቱ አጋማሽ ፋሲል ከነማን ሲገጥሙ ጉዳት ያስተናገደው ማራኪ ወርቁ እንዲሁም አስፈላጊውን የልምምድ ጊዜ በሚገባ አሟልቶ ባለመስራቱ ወደ ወላይታ ያልተጓዘው እንዳለ ደባልቄም ቡድኑን አያገለግሉም።
የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች
– ቡድኖቹ የመጀመሪያ የእርስ በርስ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
– ወላይታ ድቻ ካሉት አስር ነጥቦች ውስጥ ስምንቱን ሶዶ ላይ የሰበሰበ ሲሆን ከአራት ጨዋታዎች ሁለት አሸንፎ ሁለቱን አቻ ሲለያይ ሽንፈት አላስተናገደም። ቡድኑ አቻ የወጣውም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ነበር።
– አራት ጊዜ ከሜዳው የወጣው ባህር ዳር ከተማ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጉዞዎች ሙሉ ነጥብ ይዞ የተመለሰ ሲሆን በቀጣዮቹ ሁለት ጨዋታዎች ግን ለመሸነፍ ተገዷል።
ዳኛ
– ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ ዳዊት አሳምነው የሚመራ ይሆናል። አርቢትሩ እስካሁን በአምስት ጨዋታዎች አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔ ሲያሳልፍ አንድ የቀይ እና 15 የቢጫ ካርዶች መዟል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ወላይታ ድቻ (4-1-3-2)
ታሪክ ጌትነት
እሸቱ መና – ዐወል አብደላ – ውብሸት ዓለማየሁ – ኄኖክ አርፌጮ
በረከት ወልዴ
ቸርነት ጉግሳ – አብዱልሰመድ ዓሊ – ሳምሶን ቆልቻ
አንዱዓለም ንጉሴ – ባዬ ገዛኸኝ
ባህርዳር ከተማ (4-3-3)
ሐሪሰን ሄሱ
ሣለአምላክ ተገኝ – ወንድሜነህ ደረጄ – አቤል ውዱ – አስናቀ ሞገስ
ደረጄ መንግስቱ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ኤልያስ አህመድ
ወሰኑ ዓሊ – ጃኮ አራፋት – ግርማ ዲሳሳ