በግብፅ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ የሚጀምርበት ቀን በአንድ ሳምንት መራዘሙን ካፍ አስታወቀ፡፡
ከሰኔ 8 እስከ ሐምሌ 6 እንዲደረግ መርሀ-ግብር ተይዞለት የነበረው የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሩ ከሰኔ 14 እስከ ሐምሌ 12 እንዲካሄድ ተወስኗል፡፡ ካፍ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የቅዱስ ረመዳን ወርን አስመልክቶ የሰሜን አፍሪካ ሀገራት ተጫዋቾቻቸው ከጾሙ መጠናቀቅ በኋላ እረፍት እንዲያገኙ ያቀረቡት ጥያቄ በካፍ ተቀባይነት በማግኘቱ እንደሆነ የውድድሩ ዳይሬክተር መሐመድ ፋዲ ተናግረዋል። የውድድሩ የዕጣ ማውጣት ስነ-ስርዓት ሚያዝያ 4 እንደሚደረግም ታውቋል።
ከ2010 ወዲህ በቅድሚያ እንዲያስተናግዱ እድል ከተሰጣቸው ሀገራት እየተነጠቀ ለሌላ ሀገር ሲሰጥ የቆየው የአፍሪካ ዋንጫ ዘንድሮም ከካሜሩን ተነጥቆ ለአራተኛ ጊዜ ለማስተናገድ ለተሰናዳችው ግብፅ የተሰጠ ሲሆን በውድድሩ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በ24 ሀገራት እና በፈረንጆች ዓመት አጋማሽ የሚደረግ ይሆናል።