ደደቢት ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ቡድኑን በአሰልጣኝነት ሲመሩ የቆዩት ኤልያስ ኢብራሂም እና ጌቱ ተሾመን አሰናበተ።
በዘንድሮው የውድድር ዓመት ከዚ በፊት ሲጠቀምበት የነበረውን አካሄዱን ቀይሮ በአንፃራዊ ዝቅተኛ ደሞዝ ተጫዋቾችን በማስፈረም በፕሪምየር ሊጉ እየተሳተፈ የሚገኘው ደደቢት በውጤት ማጣት ምክንያት ሁለቱም አሰልጣኞቹን ማሰናበቱ ታውቋል። በትግራይ ዋንጫ ላይ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አሳይቶ ዓመቱን የጀመረው ደደቢት ምንም እንኳ በርካታ ተስፋዎች ቢያሳይም ቡድኑ ካደረጋቸው 12 የሊግ ጨዋታዎች ማግኘት የቻለው አንድ ድል እና አራት ነጥቦች ብቻ ሲሆን 13 የግብ እዳዎችን ይዞ በሰንጠረዡ ግርጌ ላይም ለመቀመጥ ተገዷል።
የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አማካይ ጌቱ ተሾመ ባለፈው ዓመት የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታን ድንገተኛ ህልፈት ተከትሎ ቡድኑን በጊዜያዊነት በመረከብ ከደብሮም ሀጎስ ጋር በጋራ እየመራ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን በክለቡ ያለፉትን ዓመታት የቆየው ኤልያስ ኢብራሒም ደግሞ ከተበተነው የሴቶች ቡድን ነበር ወደ ዋናው ቡድን ከተሸጋገረ በኋላ ሁለሁ አሰልጣኞች የዘንድሮውን ቡድን ተረክበው ሲሰሩ ቆይተዋል።
ደደቢት በጊያዊነት የመቐለ 70 እንደርታ እና አማራ ውሃ ስራ አሰልጣኝ የነበረው፤ በዚህ ዓመት ደግሞ በደደቢት የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ሆኖ ሲሰራ የቆየው ይድነቃቸው ዓለሙን በዋና አሰልጣኝ ቦታ ላይ ተክቷል።.