ለወራት ከሜዳ የራቀው ተስፋዬ አለባቸው ስላለበት ወቅታዊ ሁኔታ እና ቀጣይ እቅዱ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።
በ2003 ሰበታ ከተማን ለቆ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ካመራ በኋላ በክለቡ መልካም የውድድር ጊዜያት በማሳለፍ አምና ነበር ወልዲያን የተቀላቀለው። ሆኖም በአብዛኛዎቹ ጨዋታዎች በጉዳት ምክንያት ሳይጫወት የቀረ ሲሆን ሰኔ 9 ቀን 2010 ቡድኑ በጅማ አባ ጅፋር 2-0 ተሸንፎ መውረዱን ባረጋገጠበት ጨዋታ ላይ በጉዳት ከሜዳ ተቀይሮ ከወጣ በኋላ ወደ ጨዋታ አልተመለሰም። ዋና እና ምክትል አሰልጣኞቹ ከቡድኑ ጋር በተለያዩበት ወቅት ቡድኑን በአሰልጣኝነት ሲመራ የነበረው ተስፋዬ ከወልዲያ መውረድ በኋላ በሌላ ክለብ ማልያ ይታያል ተብሎ ቢጠበቅም በየትኛውም ክለብ ሳይጫወት ለወራት ያህል ከሜዳ ርቋል። ይህን ተከትሎ ተስፋዬ የት ነው ? ለሚለው ጥያቄ ሶከር ኢትዮጵያ ከተጫዋቹ ምላሽ አግኝታለች።
“በወልዲያ ዓምና ያሳለፍኩት ጊዜ በጣም የሚያሳዝን፣ የሚያበሳጭ እና የሚያቃጥል ጊዜ ነበር። ትልቁ ስህተት ደግሞ ክለቡን መያዝ ያለበት ሰው አልያዘውም። በአግባቡ ሁሉ ነገር መጀመርያ ሳይከናወን በመቅረቱ ነው ወልዲያ ለዚህ ሁሉ ነገር የተዳረገው። ከዚያ በኋላ ለመጫወት ሞራልም አልነበረኝም፤ እረፍትም ለማድረግ አስቤ ነበር ያለፉትን ወራት ከሜዳ የራቅኩት። የወልዲያ ህዝብ እግርኳስ ይወዳል። በቅርቡ ዳግመኛ ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ይመለሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለው። ሌላው በተወሰነ መልኩ እግሬ ላይ ጉዳት አጋጥሞኝ አሞኝ ስለነበረ ከእርሱም እስካገግም ድረስ ነው ከዕይታ የራቅኹት። አሁን በጣም ደህና ነኝ፤ ከፈጣሪ ጋር የአንደኛው ዙር ተጠናቆ የዝውውር መስኮቱ ሲከፈት ወደ ሜዳ እመለሳለው። የመጫወቱ አቅሙ፣ ጉልበቱም አለኝ እድሜዬም ገና ነው” ብሏል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡