በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት አዳማ አበበ ቢቂላ ስታድየም ላይ አዳማ ከተማን ከ ወላይታ ድቻ ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
አዳማ ከተማ ወደ ጎንደር አቅንቶ ከፋሲል ከነማ ጋር ያለ ግብ በአቻ ውጤት አጠናቆ ከተመለሰው የመጀመርያ አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ በዐመለ ሚልኪያስ እና ዳዋ ሆቴሳ ምትክ ሱራፌል ዳንኤል እና በሙሉቀን ታሪኩ ተሰልፈዋል። ወላይታ ድቻ በአንፃሩ በሜዳው ከባህር ዳር ከተማ ጋር አንድ አቻ ከተለያየበት ስብስቡ ሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርጓል። ታሪክ ጌትነት፣ ዐወል አብደላ እና ባዬ ገዛኸኝን ሲያሳርፍ መኳንንት አሸናፊ፣ ተክሉ ታፈሰ እና ኃይማኖት ወርቁን ወደ ሜዳ አስገብተዋል።
ኢንተርናሽናል ዳኛ አማኑኤል ኃ/ሥላሴ በጥሩ ብቃት ጨዋታውን ተቆጣጥሮ በወጣበት በዚህ ጨዋታ እንግዶቹ ወላይታ ድቻ አጥቂያቸው ሳምሶን ቆልቻን ብቻውን ከፊት በማድረግ የሱን ፍጥነት ለመጠቀም ያሰቡ በሚመሰል አጨዋወት ሌሎቹ ተጫዋቾችን በራሳቸው ሜዳ በመገደብ በሚገኙ አጋጣሚዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት መከተላቸው አዳማዎችን በተደጋጋሚ ወደ ፊት እንዲሄዱ አድርጓቸዋል። በዚህ ሁኔታ በሁለት አጋጣሚ 5ኛው እና 7ኛው ደቂቃ ላይ ሙሉቀን ታሪኩ እና ከነዓን ማርክነህ ወደ ፊት የተጣለ ነፃ ኳስ ቢያገኙም የድቻው ግብጠባቂ መኳንንት በፍጥነት ቀድሞ በመውጣት አዳነባቸው እንጂ አስፈሪ ማጥቃት ዕድሎች ነበሩ። በቀጣይ ደቂቃዎች የድቻ አማካዮች በየትኛውም አጋጣሚ እግራቸው የገባችን ኳስ በሁለቱም መስመር ለሚጫወቱት የመስመር አጥቂዎቻቸው ኳሱን በመጣል በተለይ ቸርነት ጉጉሳ በግሉ የሚያደርገው እንቅስቃሴ የአዳማን ተከላካዮች ይረብሽ እንጂ ጠንከር ያለ የጎል ሙከራ መፍጠር አልቻሉም።
ጨዋታው ቀዝቀዝ እያለ ቢሄድም ኳስን አደራጅተው ወደ ወለይታ ድቻ የግብ ክልል ለመድረስ የሚሞክሩት አዳማዎች ይህ ነው የሚባል ለጎል የቀረበ ሙከራ ባያደርጉም ብልጫ መውሰድ ችለዋል። በጥንቃቄ በመከላከል ኳስ ሲያገኙ በፍጥነት ወደ ፊት መሄድ የሚሞክሩት ድቻዎች አንድም ለጎል የቀረበ ግልፅ የግብ ዕድል ማግኘት ግን አልቻሉም። ተመሳሳይ በሆነ አጨዋወት ሁለቱም ቡድኖች መከተላቸው ወደ አሰልቺ አጨዋወት እና ወደ ጉሽሚያ ጨዋታውም አምርቶ ለእረፍት ወደ መልበሻ አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ አዳማዎች ወደ ፊት ተጭነው ተጫውተው 54ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ የተሰጠውን ቅጣት ምት በረከት ደስታ አክርሮ ቢመታውም ግብጠባቂው መኳንንት አድኖበታል። የጎል ዕድል ለመፍጠር መስመሩን በተደጋጋሚ ይጠቀሙ የነበሩት አዳማዎች 56ኛው ደቂቃ ሱሌይማን ሰሚድ በቀኝ መስመር ሳጥን ውስጥ ለማቀበል በሚመሰል መልኩ አክርሮ ወደ ጎል የመታውን ኳስ በድጋሚ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ግብጠባቂው መኳንንት እንደምንም አድኖበታል።
የተጫዋች ቅያሪ በቡድኑ የማጥቃት ሽግግሩ ላይ ለውጥ ባያመጣም ሱሌይማን ሰሚድን በኤፍሬም ዘካርያስ በመቀየር ሱራፌል ዳንኤልን በማጥቃቱም ወደ ኋላም ተመልሶ በመከላከሉ ረገድም ቡድኑን እንዲያግዝ በማድረግ የአማካይ ቁጥራቸውን አብዝተው ከነዓን ከሙሉቀን ጋር የፊት አጥቂ አድርገው ያጣመሩት አዳማዎች ኳሱን ይዘው ቢጫወቱም ብልጫ ከመውሰድ ያለፈ የድቻዎችን ጠንካራ ተከላካይ ክፍል ሰብሮ ገብቶ ያለቀለት የሚባል የግብ ዕድል ሳይፋጥሩ ቀርተዋል። እንዳገኙት በርከት ያለ የማዕዘን ምትም አንዱንም ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።
የጨዋታው የመጨረሻ አስራ አምስት ደቂቃ ድራማዊ ትዕይንት የታየበት ሆኖ አልፏል። 79ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ ከቀኝ መስመር ወደ ጎል ለማሻማት የመታውን ኳስ ሄኖክ አርፊጮ በድቻ የግብ ክልል ውስጥ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ከነዓን ማርክነህ ወደ ጎልነት ቀይሮ አዳማዎችን መሪ ማድረግ ችሏል።
ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት አዳማዎች በጥንቃቄ በራሳቸው ሜዳ ክፍል ኳሱን በመቀባበል እና አልፎ አልፎ ወደ ፊት ለመሄድ ሲሞክሩ የተስተዋለ ሲሆን ድቻዎች በበኩላቸው ጎሉ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸው በ89ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ ከቸርነት ጉግሳ የተቀበለውን ኳስ ጉልበቱን እና ፍጥነቱን ተጠቀሞ ወደ ፊት በመግፋት ተከላካዮቹን አልፎ ማስቆጠር ችሏል።
ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ አዳማ ከተማ በ20 ነጥቦች 7ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ወላይታ ድቻ በ12 ነጥቦች 11ኛ ላይ ተቀምጧል።