በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት አዳማ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ ያደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሲሳይ አብርሃ – አዳማ ከተማ
ስለጨዋታው
ጨዋታውን እንዳያችሁት ነው፤ ብዙም የምለው የለም። ከአንድ አንድ አገኙ እሷንም አገቡ። ኳስ ነው ምንም አልልም፤ ስለ ቀጣዩ ነው የማስበው። ተጫዋቾቹ የሚችሉትን ሁሉ ነገር አድርገዋል። እንዲህ ያለ ነገር ያጋጥማል። ግን በቡድኑ እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ። በሁሉም መንገድ ጎል ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል፣ ኳሱን በሚገባ ተቆጣጥረው ተጫውተዋል፣ የግብ ዕድል ፈጥረዋል። ሆኖም ያገኘነውን ዕድል አልተጠቀምንም። በቃ ኳስ እንዲህ ነው። ዛሬ ፈጣሪ ያዘዘው ሆኗል።
የግብ አጋጣሚን ያለመጠቀም ችግር
ይህን ለማሻሻል ሁሌም መስራት ይጠበቅብናል። እግርኳስ ሁሌም ስህተት ያለው ነው። በጨዋታ በልምምድ እያስተካከልከው ትሄዳለህ። ይህ ደግሞ የሀገሪቱም ችግር ነው። ሳላዲን ሰዒድ ከዓመት ጉዳት በኋላ አሁን መጥቶ በየጨዋታው እያገባ ነው። ያው መስራት ነው። ነገ ጎል ስለሚያስቆጥሩበት መንገድ ማሰራቱ ነው የሚሻለው። ስሜታዊ ስለሚሆኑ ወጣቶች በመሆናቸው ማሸነፍ ከመፈለጋቸው ፍላጎት የተነሳ የሚፈጠሩ ክፍተት ነው።
የአጥቂው ዳዋ ሆቴሳ አለመኖር
የእሱ አለመኖር እንደሚጎዳን ምንም ጥያቄ የለውም። ዳዋ እኮ የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪዎች ውስጥ ያለ ተጫዋች ነው። እርሱ ቢኖር ጥሩ ነበር ባሉትም ተጫዋቾች ቢሆንም ያገኘነውን አጋጣሚ ስተናል። ምን ይደረጋል፤ በኳስ እንዲህ ያለ ነገር ያጋጥማል። ስለዚህ ብናወራ ትርጉም የለውም። ስለ ቀጣይ ብናወራ ይሻላል። ይህ አስተማሪ ሆኖ ማለፍ አለበት ።
ዘነበ ፍስሐ – ወላይታ ድቻ
ስለ ጨዋታው
ጨዋታው በጣም ጠንካራ ነበር። አዳማም ጠንካራ ቡድን ነው። እኛም የራሳችንን ጠንካራ ጎን ይዘን ለመቋቋም ብዙ ጥረት አድርገናል። ጨዋታው ከሞላ ጎደል በሁለቱም በኩል ጥሩ ሆኖ አልፏል።
ስለ ባየ ገዛኸኝ በመጀመርያ አሰላለፍ አለመካተት
ባዬ ተጠባባቂ ወንበር ላይ የተቀመጠው ባለፈው ጨዋታ ላይ መጠነኛ ጉዳት አስተናግዶ ስለነበር ነው። ዛሬም ከጉዳቱ ትንሽ እረፍት እንዲያደርግ አስበን ነበር ያስቀመጥነው። ሆኖም ጨዋታው ጠንከር ሲል እና ውጤቱን ከመፈለግ አኳያ መጨረሻ ደቂቃ ላይ ቀይሬ አስገብቸዋለው። ውጤታማ ሆኗል፤ ተቀይሮ ገብቶም ጥሩ መንቀሳቀስም ችሏል።
ስለተከተሉት የመልሶ ማጥቃት አቀራረብ
እኛ አስበን የገባነው በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት አልነበረም። ኳሱን ይዘን ለመጫወት ነው ጥረት ያደረግነው። እኛ ይዘነው የገባነውን አጨዋወት ግን የአዳማ አጨዋወት አበላሽቶብናል። እንደምታዩት አዳማ ልምድ ያላቸውና በወጣቶች የተሞላ ስብስብ ነው። የእኔ ቡድን የተገነባው የተወሰኑት ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች ነው። ያም ሆኖ በመልሶ ማጥቃት ሳይሆን ኳሱን ተጫውቶ ጎል ለማስቆጠር ነው የገባነው። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ጎሉን ያስቆጠርንበት መንገድ በጨዋታ የሄደ መሆኑ ነው። ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት አስበን አልመጣንም፤ ከመጀመርያውም አሸንፈን ለመውጣት ነው የፈለግነው። እኛ ያለነው አጣብቂኝ ውስጥ ስለሆነ ግን አልተሳካልንም።
ከሜዳው ውጪ እስካሁን ሦስት ነጥብ ስላለማግኘቱ
ምንግዜም ለማሸነፍ ነው የምንገባው፤ ሜዳ ውስጥ ከገባን በኋላ ግን ብዙ ነገር ያጋጥመናል። ቡድኔ ጥሩ ነው፤ ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ ነው። ወደ ፊት ከሜዳ ውጭ አሸንፈን ነጥብ ይዘን እንወጣለን የሚል እምነት አለኝ። አሁን ላይ ቡድኑ ላይ የሚታይ ለውጥ ግን በጣም ጥሩ ነው።