የአሰልጣኞች አስተያየት | መቐለ 70 እንደርታ 1-0 ፋሲል ከነማ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታ ከ ፋሲል ከነማ ካደረጉት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞችን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

” ዛሬ እንደ ትልቅ ቡድን ነው የተጫወትነው ገብረመድኅን ኃይሌ – መቐለ
ስለ ድላቸው

” ማሸነፋችን እና የአሸናፊነት መንፈሳችንን ማስቀጠላችን ትልቁ ነገር ነው። በአጠቃላይ ሲታይ ውድድሩ ከባድ ነበር። ተጋጣምያችንም የቅርብ ተፎካካርያችን ስለሆነ ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ይዞ መውጣት በጣም ጥሩ ነው። ቡድኑ ስታየው የተጠናከረ ነው እና ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ትልቅ ነገር ነው። የአሸናፊነት መንፈሱንም እናስቀጥላለን። ”

ቡድኑ ተከታታይ ድል ስለ ማስመዝገቡ

‘ የአሸናፊነታችን ምስጢር ደጋፊያችን ነው። ደጋፊዎቻችን ኃይላችን ናቸው። እንደ አስራ አንደኛ ተጫዋቻችን ነው፤ እንደምታዩት እስካሁን ድጋፍ እየሰጠን ነው። የደጋፊያችን ኃይል ቀላል አይደለም። ከዛ ውጪ ደግሞ በሜዳህ የምታደርገውን ጨዋታ በደጋፊህ ታግዘህ በጥሩ መንፈስ ማሸነፍ በቀጣይ በብዙ ረገድ ስለሚያግዝህ እዛ ላይ በጥልቀት እየሰራንበት ነው። ከሜዳችን ውጭ ለማሸነፍም ጥረት እያደረግን ነው። ግን እንደሜዳችን አይደለም። በአጠቃላይ ስናየው ግን የደጋፊያችን ኃይል በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም። ”

ስለ ሁለተኛው አጋማሽ የአጨዋወታቸው ፍጥነት እና ቀጣይነቱ

” በመጀመርያው አጋማሽ ትንሽ መበታተን ነበር፤ የትኩረት እና አደረጃጀታችን የቅንጅት ችግር ነበር። ከዕረፍት በኃላ ለማስተካከል ሞክረናል። በሁለተኛው አጋማሽ ተጫዋቾቻችን ለአጨዋወታችን ታክቲክ ተገዢ እንዲሆኑ አዘን ተግባራዊም አድርገውታል። ቡድኑ እስካሁን ሳይሸነፍ ስድስት ጨዋታዎች ተጉዟል። ይህ ጥሩ ነገር ነው ለቀጣይም የሞራል ስንቅ ይሆነናል። ዛሬ እንደ ትልቅ ቡድን ነው የተጫወትነው። ”

ስለ ዳኝነት

” ምንም የምለው ነገር የለም። ”

” በኔ በኩል ጎሉ የተቆጠረበት መንገድ ትክክል አይደለም” ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ

ስለ ጨዋታው

” ጠንካራ ጨዋታ ነው የነበረው። በሁለታችንም በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ ነበር። በተለይም በመጀመርያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች በርካታ ዕድሎች ፈጥረናል። ጥሩ ነው የተንቀሳቀስነው፤ ጎል አለማግባታችን ነው ክፍተታችን። ”

ስለ ስታድየም ድባብ

” ደጋፊው ክለቡን ለመደገፍ ነው የገባው። ጥሩ ድጋፍ ነው የነበረው። ለኛ ብዙ የደጋፊ ጫና አልነበረብንም። ምክንያቱም በተለምዶ እኛ ሃገር ደጋፊ የሚጮኸው ቡድኑ ጥሩ ሲንቀሳቀስ ነው። ሜዳ ላይ ያለው እና ደጋፊው ለማለያየት የራስህ ቡድን ጥሩ መሆን አለበት። ጥሩ ኳስ ተቆጣጥረን ስለተጫወትን ብዙ የደጋፊ ጩኸት የሰማሁት በኋላ ላይ ነው። ከጎሉ በኃላ ጥሩ ድጋፍ ነበራቸው በርግጥ ግን እኛን የሚያውክ አልነበረም። ”

ስለ ዳኝነት

” ዳኝነት እንደ ዕይታህ ነው። ግን በኔ በኩል ጎሉ የተቆጠረበት መንገድ ትክክል አይደለም። ምክንያቱም ግብ ጠባቂው በራሱ ቦታ ኳሱን ለመያዝ ዘሎ ኳሱንም ይዞት ነበር። ተገፍቶ ሚዛኑን አሳጥቶታል። እዛ ቦታ ላይ ሊጠብቀው ይገባል። ይሄን በግልፅ ያያል፤ ይሄን ለምን መወሰን እንዳቃተው አላውቅም።

” ከዛ በኋላም ጎል ማስቆጠር ችለናል። ይሄኛውን በድፍረት የምናገረው ለኔ ቅርብ ቦታ ስለሆነ ነው። ከገባብን በኃላ አግብተናል ከጨዋታ ውጭ ነው ተብሎ ተሽሯል። ነው አደለም ለዛኛው መስመር ዳኛ ስለሚቀርብ ለኔ ይሄን መወሰን ይከብዳል። ይሄኛው ግን ግልፅ ውሳኔው ነው። ተገቢ ነው ብዬ አላስብም። ”

ስለ ዋንጫ ፉክክር

” ዛሬ እንደ ትልቅ ቡድን ነው የተጫወትነው። ደረጃችንን ለቀናል ብዬ አላስብም። አጥቅተናል፤ ጥሩ ጨዋታ ተጫውተናል፤ ለማሸነፍ ተጫውተናል። ቀጣይም ጨዋታዎች ለማሸነፍ ነው የምንዘጋጀው። ”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *