ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ ግስጋሴውን ባህርዳር ከተማን በመርታት ቀጥሏል

በ5ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ ግብር ትግራይ ስታድየም ላይ ባህርዳር ከተማን ያስተናገዱት “ምዓም አናብስት” በኦሴይ ማውሊ ብቸኛ ግብ 1-0 በማሸነፍ ተከታታይ ድላቸውን ስምንት አድርሰዋል።

መቐለዎች ባለፈው ሳምንት ድሬዳዋን ካሸነፈው ስብስባቸው አንተነህ ገብረክርስቶስ እና ቢያድግልኝ ኤልያስን በያሬድ ሐሰን እና ሥዩም ተስፋዬ ተክተው ወደ ሜዳ ሲገቡ እንግዶቹ የጣና ሞገዶች በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ግርማ ዲሳሳ፣ ፍቅረሚካኤል ዓለሙ እና ዳግማዊ ሙልጌታን በማሳረፍ በዳንኤል ኃይሉ፣ አሌክስ አሙዙ እና ጃኮ አራፋት ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

እጅግ አስገራሚ በሆነ የስቴድየም ድባብ የጀመረው ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር እና በቁጥር እጅግ ብዙ ሙከራዎች የታዩበት ነበር። በመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች የጣና ሞገዶች ብልጫ ሲታይበት ሞገዶቹ በርካታ የግብ ሙከራዎች ያደረጉበትም ነበር ፤ በተለይም ወሰኑ ዓሊ በሁለት አጋጣሚ ከርቀት ሞክሮ ፍሊፕ ኦቮኖ ያደነበት እና ሳለዓምላክ ተገኘ እና ኤልያስ መሐመድ ያደረጓቸው ሙከራዎች ባህርዳሮች ከፈጥሯዋቸው ዕድሎች የተሻለ ወደ ግብ የቀረቡ ነበሩ።

ቀስ ቀስ ወደ ጨዋታው ቅኝት የገቡት ባለሜዳዎቹ መቐለዎች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ምንም እንኳ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ባይደርሱም በዮናስ ገረመው እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገው ነበር። አማኑኤል ገብረሚካኤል ያሻገረውን ኳስ ከግቡ ቅርብ ርቀት ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ዮናስ ገረመው መቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ምዓም አናብስት በአሌክስ ተስማ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል ያደረጓቸው ሙከራዎች ተጠቃሾች ናቸው። በተለይም አማኑኤል ከኦሴይ ማውሊ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት እና ሃሪሰን ሄሱ ያዳናት ኳስ ለግብ የቀረበች ነበረች። 13ኛው ደቂቃ ላይም በተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር ልቀው የነበሩት መቐለዎች በየወደ ቀኝ ባደላ እንቅስቃሴ የተቀባበሉትን ኳስ አማኑኤል ገብረሚካኤል ተቆጣጥሮ ያሻማውን ኳስ በተከለላካዮች መሐል የነበረው ኦሴይ ማውሊ አስቆጥሮ ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ አድርጓል።

ከግብ በኃላ በነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴ ምንም እንኳ ተመጣጣኝ ፉክክር ቢታይበትም መቐለዎች ተደጋጋሚ ግዜ የተጋጣሚን ግብ የፈተሹበት በአንፃሩ ባህርዳሮች ደግሞ ጥቂት የግብ ዕድሎች የፈጠሩበት ነበር። በመቐለዎች በኩል ሥዩም ተስፋዬ ከሚካኤል ደስታ የተሻማውን የማዓዝን በግንባሩ ገጭቶ የወጣበት እና ኦሴይ ማውሊ ከርቀት ሞክሯት ሃሪሰን ሄሱ በሚያስደንቅ ብቃት ያወጣት ለግብ የቀረቡ ነበሩ። በአንፃሩ ጥቂት ሙከራዎች ያደረጉት የጣና ሞገዶቹ በወሰኑ ዓሊ እና ኤልያስ መሓመድ ሙከራዎች አድርገው ነበር በተለይም ኤልያስ መሓመድ መቷት ፍሊፕ ኦቮኖ ያዳናት ባህርዳሮችን አቻ ለማድረድ የተቃረበች ነበረች።

ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በአንፃራዊነት ጥቂት ሙከራዎች የታየበት ነበር። ያሬድ ከበደ ከጋብርኤል አህመድ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ በጥሩ ሁኔታ ይዞ ገብቶ መቶ የግቡን ቋሚ በመለሰበት ሙከራ ጥቃታቸው የጀመሩው ምዓም አናብስት በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በርካታ ዕድሎች አምክነዋል። በተለይም ዮናስ ገረመው ከ መዐዝን አሻምቶት ጋብርኤል መሓመድ ገጭቶ የባህርዳር ተከላካዮች ተረባርበው ያወጡት እና ያሬድ ከበደ ከጠበበ አቅጣጫ መቶ ሃሪሰን ሄሱ በድንቅ ብቃት ያወጣው ሙከራ የመቐለን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ ከተቃረቡት ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።

በሁለቱም የመስመር ተጫዋቾቻቸው ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ባህርዳሮች በበኩላቸው በዜናው ፈረደ እና ጃኮ አረፋት ሙከራዎች ማድረግ ችለው ነበር። ጃኮ አረፋት ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረጋት ሙከራ የተሻለ ለግብ የቀረበች ስትሆን ከዚ ውጭ ዳግማዊ ሙሉጌታ ግብ ጠባቂው የተፋውን ኳስ የሞከረው ሙከራም ተጠቃሽ ነው።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች ቀይረው በማስገባት ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ተጠግተው የተጫወቱት ባህርዳሮች ጫና ፈጥረው በመጫወት ሁለት ያለቀላቸው ሙከራዎች አድርገው ነበር። በተለይም ሳላምላክ ተገኘ በጥሩ ሁኔታ አሻምቶ ጃኮ አራፋት ከመግጨቱ በፊት ፍሊፕ ኦቮኖ በሚያስደንቅ ብቃት ያወጣው የማታ ማታ ባህርዳሮችን አቻ ለማድረግ የተቃረበች ነበረች።

መቐለዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በአማኑኤል ገብረሚካኤል በመልሶ ማጥቃት ሁለት ዕድሎች ፈጥረው አጥቂው ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል። በተለይም ከሃሪሰን ሄሱ አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ያመከናት በመቐለዎች በኩል አስቆጪ ነበረች።

ውጤቱ በዚ መልኩ መጠናቀቁ ተከትሎ መቐለዎች ስምንተኛ ድላቸው አስመዝግበው መሪነታቸው ሲያጠናክሩ ባህርዳሮች ወደ መሪዎቹን ለመጠጋት የነበራቸው ዕድል አምክነዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *