ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ መከላከያ

ጅማ አባ ጅፋር እና መከላከያን በሚያገናኘው የፕሪምየር ሊጉ ተስተካካይ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

በሁለተኛው ሳምንት የሊጉ መርሐ ግብር ውስጥ የነበረው የሁለቱ የዘንድሮ የአፍሪካ መድርክ ተሳታፊዎች ጨዋታ ነገ 09፡00 ላይ በጅማ ይካሄዳል። 13ኛ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ቻምፒዮኖቹ በደቡብ ፖሊስ ከደረሰባቸው አሰቃቂ ሽንፈት ያገገሙበትን የ1-0 ድል በደደቢት ላይ ካስመዘገቡ በኋላ እዛው ሜዳቸው ላይ መከላከያን ያስተናግዳሉ። ጅማዎች በቀደሙት ጨዋታዎቻቸው ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ደካመ መሆን ወደ ሊጉ አናት የመድረስ ህልማቸውን ቢያስቀረውም አሁንም እስከ ሦስተኛ ደረጃ ይዘው የመጀመሪያውን ዙር መጨረስ የሚችሉበት ዕድል አለ። አባ ጅፋሮች ከግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ እና በደደቢቱ ጨዋታ ጉዳት ገጥሞት ለመቀየር ከተገደደው ኤልያስ አታሮ ውጪ ቀሪው ስብስባቸው ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሆኗል።

የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታውን የሚያከናውነው መከላከያ አንድ ደረጃ የመሻሻል ተስፋ አለው። የአሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቡድን ሁለት ተከታታይ ድሎችን አሳክቶ ካገገመ በኋላ በብዙው ብልጫ በወሰደበት የድሬዳዋው ጨዋታ ማሸነፍ አለመቻሉ በ22 ነጥብ በሊጉ ወገብ ወደሚገኙት ሦስት ክለቦች መቅረብ የሚችልበትን ዕድል አስመልጦታል። ሆኖም በሊጉ በርካታ (26) ግቦችን በማስተናገድ ቀዳሚ ለሆነው ክለብ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች መረቡ አለመደፈሩ በመልካምነት የሚነሳ ነው። መከላከያ ለነገው ጨዋታ ዳዊት እስጢፋኖስ እና ፍፁም ገብረማርያምን ጨምሮ ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ያላገገመው ታፈሰ ሰረካን ወደ ጅማ ይዞ አልተጓዘም።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ጅማ አባ ጅፋር የሊጉን በተቀላቀለበት እና ዋንጫ ባነሰበት የአምናው የውድድር ዓመት በሜዳው ከመከላከያ ጋር በ 1-1 ውጤት ነጥብ ሲጋራ አዲስ አበባ ላይ ደግሞ 1-0 ማሸነፍ ችሏል። የዚህን ጨዋታ ብቸኛ ግብ ያስቆጠረውም የያኔው የጅማ የአሁኑ ደግሞ የመከላከያ አጥቂ ተመስገን ገብረኪዳን ነበር።

– በሜዳው አምስት ጨዋታዎችን ያደረገው ጅማ አባ ጅፋር ሦስቱን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ በሁለቱ ድል ቀንቶታል ፤ ከአምና ጀምሮም በሜዳው ለ18 ጨዋታዎች ያለሽንፈት በመጓዝ ላይ ይገኛል።

– ስድስት ጊዜ ከአዲስ እበባ የወጣው መከላከያ በመጀመሪያ እና በመጨረሻው የሀዋሳ እና የመቐለ ጉዞው በድል ሲመለስ በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ሁለት የሽንፈት እና ሁለት የአቻ ውጤቶች ገጥመውታል።

ዳኛ

– ጨዋታው ዘንድሮ ከሁለቱ ቡድኖች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚገናኘው ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ሰባተኛው የዓመቱ ጨዋታ ይሆናል። ቴዎድሮስ እስካሁን በስድስት ጨዋታዎች 16 የቢጫ እና አንድ የቀይ ካርዶችን ሲመዝ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔም አሳልፏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

ዳንኤል አጃዬ

ዐወት ገብረሚካኤል – መላኩ ወልዴ – አዳማ ሲሶኮ – ተስፋዬ መላኩ

ይሀን እንዳሻው – ንጋቱ ገብረስላሴ – መስዑድ መሀመድ

ዲዲዬ ለብሪ – ማማዱ ሲዲቤ – አስቻለው ግርማ

መከላከያ (4-4-2 ዳይመንድ)

ይድነቃቸው ኪዳኔ

ሽመልስ ተገኝ – ምንተስኖት ከበደ – አበበ ጥላሁን – ዓለምነህ ግርማ

ቴዎድሮስ ታፈሰ

ሳሙኤል ታዬ – ዳዊት ማሞ

ፍሬው ሰለሞን

ፍቃዱ ዓለሙ – ምንይሉ ወንድሙ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *