ሴቶች 1ኛ ዲቪዝዮን | አዳማ ወደ መሪነት ከፍ ሲል ጌዴኦ ዲላ እና ሀዋሳ ከሜዳቸው ውጪ አሸንፈዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን የሁለተኛው ዙር ዛሬ በተደረጉ አምስት ጨዋታዎች ሲጀመሩ ሁሉም ጨዋታዎች በመሸናነፍ ተጠናቀዋል።

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ 11:00 የጀመረውና የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በመከላከያ እና አዳማ ከተማ መካከል ተከናውኖ በእንግዶቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። የሚቆራረጡ ቅብብሎች እና የኃይል አጨዋወቶች በበዙበት የመጀመርያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ግልፅ የጎል ማስቆጠር አጋጣሚ መፍጠር ተስኗቸው የነበረ ሲሆን መከላከያዎች ከርቀት በሚመቱ ኳሶች በተሻለ ሁኔታ ሙከራዎችን አድርገዋል። በአራተኛው ደቂቃ ሔለን እሸቱ ከሳጥኑ አቅራቢያ መትታ ግብ ጠባቂዋ እምወድሽ የያዘችባት፣ በ15ኛው ደቂቃ መሠሉ አበራ ከረጅም ርቀት የተሰጠውን ቅጣት ምት በቀጥታ ሞክራ አግዳሚው የመለሰባት እንዲሁም በ36ኛው ደቂቃ የምስራች ላቀው በተመሳሳይ ከቅጣት ምት ሞክራ ለጥቂት የወጣባት ሙከራዎች የሚጠቀሱ ነበሩ።

አዳማ ከተማዎች በሰርክአዲስ እና ሴናፍ አማካኝነት ከመከላከያ ተከላካዮች ጀርባ ያለውን ሰፊ ቦታ ለመጠቀም ያደረጉት ጥረት በሙከራ ባይታጀብም የሁለቱ እንቅስቃሴ ተጋጣሚያቸው ኳስ መስርቶ እንዳይጫወት ጫና በመፍጠር ረገድ የሳካ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ አዳማ ከተማዎች እስከ መጨረሻዎቹ 15 ደቁቃዎች ድረስ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉበት ነበር። ሆኖም በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ መሆናቸውን በግብ እድሎች ማጀብ አልቻሉም። መከላከያዎች በአንፃሩ ሔለን ሰይፉ እና መዲና አወልን ቀይረው ካስገቡ በኋላ የፊት መስመራቸውን በማጠናከር ጎል ለማስቆጠር ያቃረባቸውን እንቅስቃሴ አድርገዋል። በተለይ በ78ኛው ደቂቃ ሔለን የመታችው ኳስ የግቡን ቋሚ ሲመልሰው መዲና ብትመታውም አልፊያ የጎሉ መስመር ላይ የነበረችው አልፊያ ጃርሶ በግንባሯ ያወጣችው ጦሩን መሪ ሊያደርግ የሚችል አስቆጪ ዕድል ነበር።

የመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች በውዝግብ የተሞላ ነበር። በ80ኛው ደቂቃ ሴናፍ ዋቁማ አዳማን የድል ባለቤት ያደረገች ወሳኞ ጎል ያስቆጠረች ሲሆን መከላከያዎች ከጎሉ መቆጠር በፊት የቡድናቸው ተከላካይ ላይ ጥፋት ተፈፅሟል በሚል ቅሬታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ አሰምተዋል። ለደቂቃዎች ከቆየው ውዝግብ በኋላ ጨዋታው ቀጥሎ በ88ኛው ደቂቃ ሴናፍ ዋቁማ በግራ መስመር በኩል በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ መከላከያ የጎል ክልል ልትገባ ስትል በተሰራባት ጥፋት በድጋሚ ውዝግብ ተነስቶ አምበሏ ሳምራዊት ኃይሉ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብታለች። ከጎሉ መቆጠር ጀምሮ ስሜታዊ የነበረችው ሳምራዊት ከቀይ ካርዱ በኋላ ከዳኛ ጋር ግብግብ ለመግጠም ብትሞክርም በተጫዋቾች ጥረት ከሜዳ ልትወጣ ችላለች። ክስተቱን ተከትሎ መከላከያዎች ክስ ሲያስመዘግቡ ጨዋታውም በጭማሪ ስድስት ደቂቃዎች ለውጥ ሳይመዘገብበት በአዳማ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

አዳማ ከተማ በድሉ በመታገዝ ቅዳሜ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የሚጫወተው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በሁለት ነጥቦች በመቅደም የደረጃ ሠንጠረዡ አናት ላይ ተቀምጧል።

ድሬዳዋ ከተማ 1-2 ጌዴኦ ዲላ

(ዳንኤል መስፍን)

10:00 ላይ በጀመረው ጨዋታ ገና ከጅማሬው በ2ኛው ደቂቃ ትዝታ ፈጠነ በቀላሉ ለማቀበል ወደ ጎል ክልል የላከችውን ኳስ የጌዲዮ ዲላ ግብ ጠባቂ እና ተከላካይዋ አለመናበብን ተከትሎ በቀጥታ ጎል በመሆኑ ድሬዎች ቀዳሚ መሆን ቻሉ። ምንም እንኳ ጎሉ በስህተት ቢቆጠርባቸው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ብዙም ያልቆዩት ዲላዎች የፈጠሩት ጫና ተሳክቶላቸው 11ኛው ደቂቃ በፍጥነት ከተካላካይ ቀድማ የገባችው ረድኤት አስረሳኸኝ ባስቆጠረችው አቻ መሆን ችለዋል።

ባለሜዳዎቹ ድሬዎች ኳሰ ተቆጣጥረው ከሜዳ ክፍላቸው በመነሳት የሚያደርጉት ጥረት መልካም ቢሆንም ወደ መጨረሻው የሜዳው ክፍል ሲደርሱ ባልተረጋጋ ሁኔታ የግብ ዕድሎችን ሳይፈጥሩ በጌዲዮ ዲላ ተከላካዮች በቀላሉ ይነጠቁ ነበር። በተለይ በ11 ጎሎች የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን እየመራች የምትገኘው አይዳ ዑስማን በጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ አለመኖር የድሬዎች የማጥቃት አቅምን ቀንሶታል። በፈጣን አጥቂዎቻቸው አማካኝነት እንዲሁም በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የወደሱት ጌዲዮ ዲላዎች ከሳጥን ውጭ የሚመቱት ጠንከራ ኳስ ለግብ ጠባቂዋ ሂሩት ደሴ ፈተና ሆኖባት ነበር። በጨዋታው የመጀመርያ 11 ደቂቃ በሁለቱም በኩል ጎሎች መስተናገዳቸው እና ጨዋታ ነፃ እንቅስቃሴ የነበረበት በመሆኑ ተጨማሪ ጎሎች ይቆጠራሉ ተብሎ ቢጠበቅም ይህ ሳይሆን ዘግይቶ 36ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ቤቲ በቀለ በግንባሯ በመግጨት ግሩም ጎል አስቆጥራ ጌዲዮ ዲላዎችን መሪ እንዲሆን አስችላለች።

ከእረፍት መልስ ድሬዎች በፍጥነት የሁለት የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ የአቻ የሚሆንበት አጋጣሚ በ51ኛው ደቂቃ መቅደስ ማስረሻ ከሳጥን ውጭ በተመታ ኳስ ጥሩ የግብ ዕድል ቢፈጥሩም ግብ ጠባቂዋ ምህረት ተሰማ አድናባታለች። እንግዶቹ ጌዲዮዎች በ55ኛው ደቂቃ አማካኟ ስመኝ ምህረቴ ከሳጥን ውጭ ኳሱን በደረቷ አብርዳ አክርራ የመታችውን ግብ ጠባቂዋ ሂሩት ደሴ እንደምንም ያዳነችባት ጥሩ የጎል አጋጣሚ ነበር። በፍጥነት ወደ ጎል የሚደርሱት እና በመሐል ሜዳ ላይ ብልጫ የነበራቸው የጌዲዮዎች 58ኛው አጥቂዋ ትንቢት ሳሙኤል ከቀኝ መስመር የተጣለላትን በግንባሯ ግጭታ ለጥቂት የወጣባት ኳስ እንዲሁም እራሷ በድጋሚ 68ኛው ደቂቃ ነፃ ኳስ አግኝታ ግብጠባቂዋ ሂሩት ከግብ ክልሏ በመውጣት በጥሩ ሁኔታ ያዳነችባት ጌዲዮ የጎል መጠኑን ማስፋት የሚችሉበት ይሆን ነበር።

በዛሬው ጨዋታ ያገኘችውን የጎል እድሎች ያልተጠቀመችው የጌዲዮዋ አጥቂዎ ትንቢት ሳሙኤል 71ኛው ደቂቃ ሌላ የጎል አጋጣሚን አግኝታ አምክናለች። አልፎ አልፎም ቢሆንም ወደ ጌዲዮዎ ግብ ክልል የሚደርሱት ድሬዎች አቻ የሚሆኑበትን 76ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል የጎል ሳጥን ውስጥ በመግባት ተቀይራ በገባችው ቤቴልሔም ኪዳኔ ጥሩ ሁኔታ ኳሱን መሬት ለመሬት የመታችው ለጥቂት በግቡ አግዳሚ ጠርዝ የወጣባቸው ኳስ የሚያስቆጭ ነበር።

በመጨረሻም በቀሩት ደቂቃዎች በቆሙ ኳሶች የአቻነት ጎል ፍለጋ የሚያደርጉት ጥረት በጌዲዮ ዲላ በግብጠባቂዋ ምህረት ተሰማ ጥሩ ብቃት ምክንያት ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው በጌዲዮ ዲላ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሌሎች ጨዋታዎች

ወደ አሰላ ያቀናው ሀዋሳ ከተማ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚን 3-2 አሸንፏል። ምርቃት ፈለቀ በጨዋታ እና በፍፁም ቅጣት ምት ሁለተ ጎሎች ስታስቆጥር ካሰች ፍስሀ ቀሪዋን የሀዋሳ ከተማ ጎል አስቆጥራለች። ቅድስት በላቸው ደግሞ የሁለቱ የጥሩነሽ ዲባባ ጎሎች ባለቤት ናት።

ባህርዳር ላይ አአ ከተማን የገጠመው ጥረት ኮርፖሬት በትመር ጠንክር ሁለት እና ትዕግስት ወርቁ አንድ ጎል 3-2 ሲረቱ አርባምንጭ ላይ አርባምንጭ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን በጸጋነሽ ወረቶ ብቸኛ ጎል ያሸነፉበት ጨዋታም የዚህ ሳምንት ሌላው መርሐ ግብር ነው።

በ12ኛው ሳምንት ቀሪ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ቅዳሜ ሲጫወቱ ባንክ ማሸነፍ ከቻለ ወደ መሪነቱ የሚመለስ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *