“የስኬታችን ምስጢር ጠንክረን መስራታችን ነው” ገብረመድኅን ኃይሌ

ባለፈው ዓመት ጅማ አባጅፋር ከከፍተኛ በመጣበት ዓመት የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ ያስቻሉት እና በዚህ ዓመትም ከመቐለ 70 እንደርታ ስኬታማ የውድድር ጊዜ በማሳለፍ ሊጉን እየመሩ የመጀመርያው ዙር ማጠናቀቃቸውን ያረጋገጡት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በቡድናቸው ወቅታዊ አቋም እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ቆይታ አድርገዋል፤ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

በሊጉ ተከታታይ ስምንት ጨዋታዎች አሸንፋችኋል። ሊጉንም እየመራችሁ ነው። የስኬታችሁ ምስጢር ምንድነው?

አንደኛ ጠንክረን መስራታችን ነው። ሁለተኛው ደሞ ጨዋታዎችን ስታሸንፍም ሆነ ስትሸነፍ እንዴት ነጥቡን አመጣነው? እንዴትስ አጣነው? የሚለውን ነገር ማየት ወሳኝ ነው። ሁልጊዜም በችግሮቻችን ላይ እየሰራን ጥሩ ጉኑን ጠብቀን መሄድ ላይ ነው ያተኮርነው። ከዛ ባለፈም ሜዳችን ላይ ስንጫወት ደጋፊዎቻችን ያላቸው ሚና ላቅ ያለ ነው። የነሱ ድጋፍ እንዲሁ በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም።
ሌላው ተጫዋቾቼ ያላቸውን ነገር አውጥተው በመስጠት እና የሚሰጣቸውን ነገር በአግባቡ እና በትዕግስት በመተግበር እንዲሁም ነገሮችን ቶሎ በመቀበል ትልቅ ሚና ነበራቸው። እነዚህን ነገሮች ተደማምረው ለዚህ አብቅተውናል።

የቡድኑ የዚህ ዓመት ዕቅድ ምንድን ነው?

አሁን እያሳየነው ያለው ወጥነት ያለው ብቃት ከማሳየታችን በፊትም ዓመቱ ሲጀመር ከመጀመርያዎቹ ሶስት ቡድኖች ውስጥ አንዱ ሆኖ መጨረስ ነበር እቅዳችን። አሁንም የሚቀየር ነገር የለም።

በቡድኑ ወቅታዊ ብቃት ምንያህል ደስተኛ ነህ?

በጣም በጣም ደስተኛ ነኝ። ተጫዋቾቼ ከጎኔ ሆነው በሁሉም ረገድ መስዋዕትነት እየከፈሉ ስላሉ በጣም ደስተኛ ነኝ። ባለው የሜዳ ላይ ድጋፍም በጣም ደስተኛ ነኝ። ምንም እንኳ በአንድ ወቅት ምክንያቱ ያልታወቀ ተቃውሞ ቢኖርም ምክንያቶቹ ውጤትን ብቻ ተከትለው የመጡ ናቸው ብዬ አልገምትም፤ ምንም እንኳ ተቃሞው ቢያጋጥመንም እሱን በትዕግስት አልፈን ወደተሻለ ነገር ልንመጣ እንደምንችል ደጋግሜ እናገር ነበር። በአጠቃላይ ባለው ነገር ግን በጣም ደስተኛ ነኝ።

በዓመቱ መጀመርያ ከተከታታይ ማሸነፍ በኋላ የገጠማችሁ የውጤት መቀዛቀዝ ምክንያቱ ምንድን ነበር? በኋላስ እንዴት በፍጥነት ወደ ጥሩ ቅርፅ ልትመጡ ቻላችሁ?

አንድ ቡድን ሊያጋጥነው የሚችል ነገር ነው ያጋጠመን። አንድ ቡድን በዓመት ውስጥ ብቃቱ ጥሩ ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል። በተቃራኒው ደግሞ ሊወርድም ይችላል። በትግራይ ዋንጫ ላይ ጥሩ ነበርን። ከዛ በኋላ የወረድንበት ምክንያትም ይታወቃል። የብቃት መውረድ አያጋጥመንም ባንልም እንኳ ይህን ያክል እንወርዳለን ብለን አንገምትም አሁንም። በዛ ሰዓት የብቃታችን መውረድ ምክንያት በተደጋጋሚ የጨዋታዎች መቆራረጥ እና ከጨዋታ መራቅ ነበር ፤ እሱ በተጫዋቾቻችን ላይ የፈጠረው የስነ ልቦና እና የሞራል ችግር ነበር።

በሜዳችን መጫወት እየተገባን በተለይም የፋሲል ከነማ እና ባህር ዳር ከተማ የሜዳችን ጨዋታዎች ተዘዋውረው በተከታታይ ከሜዳችን ወጥተን እንድንጫወት በመደረጋችን በሥነ ልቦና እና በሌሎች ጉዳዮች ተፅዕኖ አለው። ቅድም እንዳልኩህ ግን አንድ ቡድን እንዲሁ በተከታታይ ብቃት ሊያስመዘግብ አይችልም። ዋናው ነገሩ እንዴት ወደ ጥሩ ብቃት መመለስ እንችላለን ነው። እንዴት ከወደቅክበት መነሳት እንዳለብህ ማወቅ አለብህ። እዛ ላይ ብዙ ችግር አልነበረንም። ቶሎ ወደ ጥሩ ብቃት ልንመጣ ችለናል።

የብቃት መውረዱ ያጋጠመን እና ሽንፈቶች እንዴት መጡ ለሚለው ሽንፈት ባጋጠመን ሜዳ ምን ችግር እንደነበረብን ለይተን እናውቀዋለን ፤ አቻ በወጣንባቸው የጨዋታዎችም በብቃት ደረጃ መጥፎ አልነበርንም። ከዛ በኃላ ባለው ጊዜ ደሞ አሸናፊነት መንፈሱን ጠብቆ ለመሄድ እየሰራን ነው የሄድነው።

በእያንዳንዱ ጨዋታ ለተጫዋቾቻችን የምናስተላልፈው ስለ ቀጣይ ጨዋታ ብቻ እንዲያስቡ ነው፤ በዛ መንገድ ነው የምንዘጋጀው። በሂሳብ ስሌት የረጅም ግዜ እቅድ እያሰብን በተጫዋቾቻችን አእምሮ ላይ ጭንቀት አንጨምርም። በዚ መንገድ የ ማሸነፍ መንፈሳችን በጥሩ ሁኔታ ላይ መድረስ ችሏል። በዚ መንገድም ነው እየሄድን ያለነው።

ውድድሩ ግማሽ ዓመት ላይ እያለ ለዋንጫ መታጨታችሁ በቀጣይ ጉዟችሁ ላይ ጫና አይፈጥርባችሁም?

ጫና ይኖረዋል። ሁሉም ቡድን በመሪው ላይ ነው ትኩረቱ። ቡድኖች በተለየ መንገድ ተዘጋጅተው ሊመጡ ይችላሉ። በሌላ መንገድም ሌላ ውጫዊ ችግር ሊኖር ይችላል፤ በዳኝነትም በሌላም በሌላም ለወደፊት የሚያጋጥምህን አታውቀውም። ስለዚህ አሁን ላይ በአንድ ጊዜ ስለ ዋንጫ በስሜት ተገፋፍተህ የምትናገረው ነገር አይደለም። አንደኛ ዙር ማለት በጣም ገና ነው፤ በዚ ሰዓት ታች ያለው ወደ ላይ ሊመጣ ይችላል። ላይ ያለው ደሞ ምንም ዋስትና የለውም፤ ሁሉም ዕድል አለው። ጥሩ ምሳሌ ለመውሰድ የማንቸስተር ሲቲን እናንሳ፤ በጣም ለብዙ ግዜ ሊጉን መርቶ ነበር አሁን ግን በሊቨርፑል ቦታው ተነጥቋል። ይህ ያጋጥማል። ነገር ግን ዋናው ነገር በችግሮችህ እየሰራህ መሄድ ለጥሩ ደረጃ ያደርስሃል።

ቅርብ ተቀናቃኞቻችሁ አንፃር ሲታይ ጠባብ ስብስብ ነው ያላችሁ። ከዛ በተጨማሪ በርካታ ተጫዋቾች ጉዳት አለባቸው። በዚ ምክንያት ወደ ዝውውር ገበያ ትገባላችሁ?

አዎ እንሳተፋለን፤ እያየን ነው ያለነው። ጥሩ ተጫዋች ካገኘን እስከ ሶስት ተጫዋቾች የማዘዋወር እቅድ አለን። በቀጣይነት አስራ አምስት የሊግ ጨዋታ እና የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታዎችም አሉብን። ይሄን ሁሉ ስታስበው ከባድ ነው። በተቻለን መጠን እየሞከርን ነው። ትኩረት የምናረገውም በሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ነው። ቡድናችን ለማጠናከር የተቻለንን እናደርጋለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *