መቐለ እና ጅማ ነገ በሚያደርጉት የመጨረሻው ተስተካካይ ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ጉዳዮች አንስተናል።
ጅማ አባ ጅፋር በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ለመልስ ጨዋታ ወደ ሞሮኮ ሲያቀና ከ11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል በተስተካካይነት የተያዘው የመቐለ እና የጅማ ጨዋታ ነገ 09፡00 ላይ በትግራይ ስታድየም ይከናወናል። የጨዋታው አሁን ላይ መደረግም ከሁለቱ ተጋጣሚዎች ባለፈ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ መቐለን በመከተል ላይ የሚገኙት ሲዳማ ፣ ጊዮርጊስ እና ፋሲልን ቀልብ ጭምር እንዲስብ ምክንያት ሆኗል።
32 ነጥብ ላይ የሚገኙት መቐለ 70 እንደርታዎች ጨዋታውን አሸንፈው ከተከታዮቻቸው ያላቸውን ነጥብ ማስፋት ከቻሉ ሁለተኛውን ዙር በተሻለ ነፃነት የመጀመር ዕድል ይኖራቸዋል። ከሰንጠረዡ አጋማሽ ተነስተው ቀስ በቀስ ወደ አንደኝነቱ የመጡት ባለሜዳዎቹ ባህር ዳርን ማሸነፍ በቻሉበት የመጨረሻው የአምስተኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታቸው ስምንተኛ ተከታታይ ድላቸውን ለማስመዝገብ ችለዋል። ከተለመደው የመጀመሪያ አሰላለፋቸው ውስጥ እንደ ሳሙኤል ሳሊሶ እና ሀይደር ሸረፋን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን በጉዳት ቢያጡም የአሰላለፍ ይዘታቸውን ሳይቀይሩ የተጨዋቾች ለውጥ እና የቤታ ሽግሽጎችን ብቻ በማድረግ መቀጠላቸው ያዋጣቸው ይመስላል። በነገውም ጨዋታ ሁለቱን ተጫዋቾች ጨምሮ አቼምፖንግ አሞስ እና አሸናፊ ሀብቱ በጉዳት ሳቢያ ቡድኑን እንደማያገለግሉ ታውቋል።
ሻምፒዮኖቹ ጅማ አባ ጅፋሮች በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች መረባቸውን ሳያስደፍሩ ነው ወደ መቐለ የተጓዙት። ከዳንኤል አጄዬ መመለስ በኋላ ወደ ቀድሞው ጥንካሬው የተመለሰው የኋላ ክፍላቸውም ቀጥተኛነት እየተነበበት የሚገኘው የተጋጣሚያቸውን ወደ ፊት የሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች በፈጣኖቹ አጥቂዎች ጥቅም ላይ ከመዋላቸው በፊት የማምከን ኃላፊነት ይኖርባቸዋል። ከመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ሰባት ነጥቦች ያሳኩት አባ ጅፋሮች 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን ነገ በድል ከተመለሱ አምና በ25 ነጥቦች 2ኛ ደረጃ ላይ ከጨረሱበት ውጤት በአንድ ነጥብ ዝቅ ብለው ግን ደግሞ በስድስተኛ ዙሩን የመጨረስ አጋጣሚው ይኖራቸዋል። በጨዋታው ቡድኑ ከግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ ጉዳት ውጪ ቀሪው ስብስቡ ከቅጣት እና ጉዳት ዜናዎች ነፃ መሆኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የእርስ በርስ ግንኙነቶችእና እውነታዎች
– በ2010 የውድድር ዓመት ሊጉን የተቀላቀሉት መቐለ እና ጅማ በተገናኙባቸው ሁለት ጨዋታዎች በየሜዳቸው የ1-0 ድልን ማሳካት ችለዋል።
– በትግራይ ስታድየም ስምንት ጨዋታዎችን ያደረገው መቐለ 70 እንደርታ ሠባቱን በድል ሲወጣ በአንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል፡፡ ከስምንቱ ተከታታይ ድሎቹ ውስጥም አምስቱ በሜዳው የተገኙ ነበሩ።
– ጅማ አባ ጅፋር እስካሁን ከሜዳው ውጪ ሰባት ጨዋታዎችን ሲያደርግ ሁለቱ የድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶችን አሳክቶ ሦስት ሽንፈቶች ገጥመውታል።
ዳኛ
– እስካሁን በተካሄዱ ጨዋታዎች ሁለቱ ቡድኖች የተሳተፉባቸውን ጨዋታዎች ያልዳኘው ተካልኝ ለማ ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የሚመራው ሲሆን በአምስት ጨዋታዎች 18 የቢጫ እና 1 የቀይ ካርዶችን ሲመዝ አንድ የፍፁም ቅጣት ምት ውሳኔም አሳልፏል።
ግምታዊ አሰላለፍ
መቐለ 70 እንደርታ (4-4-2)
ፍሊፔ ኦቮኖ
ስዩም ተስፋዬ – አሌክስ ተሰማ – አሚኑ ነስሩ – ያሬድ ሀሰን
ያሬድ ከበደ – ጋብርኤል አህመድ – ሚካኤል ደስታ – ዮናስ ገረመው
አማኑኤል ገብረሚካኤል – ኦሰይ ማወሊ
ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)
ዳንኤል አጃዬ
ዐወት ገብረሚካኤል – ከድር ኸይረዲን – አዳማ ሲሶኮ – ተስፋዬ መላኩ
ይሁን እንዳሻው – አክሊሉ ዋለልኝ – መስዑድ መሀመድ
ዲዲዬ ለብሪ – ማማዱ ሲዲቤ – አስቻለው ግርማ
© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡